የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የ"ይሆን አይሆን?" ጥያቄ አይደለም። ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የምትሆነው በስሜት ግልቢያ ሳይሆን፣ በጥልቅ ስሌት ነው። ጉልበቷን በመመካት ሳይሆን እውነትን፣ ሀቅን፣ ታሪክን፣ ማስረጃዎችን እና አካባቢያዊ የጂኦ-ፖለቲካ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ ነው። የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት በፍጹም የማያወላውል ጉዳይ ነው።
ከሁሉ በላይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ የባሕር በር ፍፁም አስፈላጊ መሆኑን በአንድ ልብ ይስማማል። ታሪካዊ መብቱን በሴራና አሻጥር በመነጠቁም ሲንገበገብ ኖሯል፣ ይህንንም የዘመናት የታሪክ ግድፈት ለማረም በአንድነት ሆ ብሎ ተነስቷል።
በሌላ በኩል፣ መላው ዓለምም ኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር ጠረፍ ሀገር ስለመሆኗ ጠንቅቆ ያውቃል፣ ይህን እውነትም ይመሰክራል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ስትሆን፣ የማንንም መብት ሳትጋፋ ከተፈጥሯዊ በሯ ጋር የመገናኘት ጥያቄን ነው ያነሳችው።
ይህ ጥያቄ በየትኛውም መመዘኛ ምክንያታዊ፣ ህጋዊ እና ተገቢ ነው። ይህ የነቃ ትውልድ ይህን ታሪካዊ ጥያቄ አያልፈውም። መብቱን ለማስመለስ ብቁ የሆነ የሥነ-ልቦና፣ የአቅም እና የዲፕሎማሲ ዝግጅት ያደረገ፣ በበቂ ሁኔታ የበሰለና የሠራ ትውልድ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትሻው የሌሎችን ሉዓላዊነት ለመጋፋት ወይም በጉልበት ለመውሰድ አስባ አይደለም። የባሕር በር ጥያቄያችን የፍትህ፣ የኅልውና እና የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው።
በታሪክ መዝገብ እንደሰፈረው፣ ከጥንታዊቷ የአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ አዱሊስን እና ሌሎችንም ስትራቴጂያዊ የባሕር በሮች ስታስተዳድር የኖረች፣ ቀይ ባሕርን ተሻግራ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለች የባሕር ባለርስት ሀገር ነበረች። ይህ ታሪካዊ ሀቅ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነት ያረጋግጣል።
ከሞራል እና ከሎጂክ አንፃር ስንመዝነው ደግሞ፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ምሰሶ የሆነች ሀገር ወደብ አልባ ሆና መቅረቷ ፍፁም ኢ-ፍትሃዊነት ነው።
የባሕር ጠረፍ አለመኖር ለአንድ ሀገር እድገት ትልቁ መዋቅራዊ ማነቆ ነው። ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት በባሕር በር እጦት ከባድ ዋጋ ከፍላለች፡፡ በመሆኑም የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን፣ የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ፣ ብሎም የቀጣናውን የኃይል ሚዛን የማስጠበቅ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የምታከብር፣ በዓለም አቀፍ የህግ መርሆዎች የምትመራ እና ለአፍሪካ ቀንድም ሆነ ለዓለም ሰላም በጎ አስተዋጽኦ የምታበረክት የሰላም መልህቅ ናት። ፍላጎቷም በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ፣ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ውኅደት የሚያፋጥን እና የጋራ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ "አሸናፊ-አሸናፊ" አካሄድ ነው። የኢትዮጵያ አቋም በጦርነት ላይ ሳይሆን፣ በማያወላውል የዲፕሎማሲ እና አብሮ የማደግ ርዕይ ላይ የተገነባ ነው።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ እና ሞራላዊ መብቷን ለማስከበር ሁለንተናዊ ዝግጅት አድርጋለች። በአንድ በኩል በቂ የሆኑ ታሪካዊ፣ ህጋዊ እና ፖለቲካዊ ማስረጃዎችን በመያዝ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ብሔራዊ ጥቅሟ ከማንኛውም የውጭ ትንኮሳ ለመከላከል የሚያስችል ዘመናዊ የባሕር ኃይል ዳግም በማደራጀት ራሷን በተጠንቀቅ አቁማለች። ይህ የተሟላ ወታደራዊ እና ተቋማዊ ቁመናዋ፣ ማዕበልን ለመግራት እና የሀገራችን መብት በውሃ አካላት ላይ ለማስከበር ያላትን ብቃት በግልፅ የሚያሳይ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ልቦና እና የተቋማት አቅም ዛሬ በአንድ ምት እየመታ ይገኛል። የትናንቱ የታሪክ ስብራት ዛሬ በተደራጀ፣ በሠለጠነ እና ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ እየተጠገነ ነው። ስለዚህ እውነታው አንድ እና የማያሻማ ነው። የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ወደ ኋላ የማይመለስ፣ ዛሬም ሆነ ነገ በተግባር የሚረጋገጥ ፍፁም እውነት ነው። ቅንጣት ታክል አትጠራጠሩ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ትሆናለች!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: