Search

የዓለምን አካሄድ የቀየረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ልዩ መንገድ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 72

በዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ታሪክ ውስጥ ሀገራዊ የምክክር መድረኮች ውስብስብ የፖለቲካ ቀውሶችን፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎችን እንዲሁም መዋቅራዊ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደ ዋነኛ የፖለቲካ መሳሪያ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በርካታ የላቲን አሜሪካ፣ የደቡብ ምስራቅ እስያ እና የአፍሪካ ሀገራት የውስጥ ግጭቶቻቸውን ለመፍታትና አዲስ ሀገራዊ ቃል-ኪዳን ለመመስረት ሀገራዊ ምክክሮችን አካሂደዋል። ሆኖም ግን፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተገበረ ያለው አካታች አሠራር ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የተለየና አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚከፍት ሆኖ ተገኝቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮችን ስንመረምር፣ ትጥቅ ያነሱ አካላት በምክክር ሂደት ውስጥ የሚሳተፉበት አሠራር ሁልጊዜም በጠበበና በጥብቅ የፖለቲካ ወይም የወታደራዊ ቅድመ-ሁኔታዎች የተገደበ ነበር።

ለምሳሌ በ1990ዎቹ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓትን ለመሻር የተካሄደው ድርድር የታጠቁ ክፍሎችንና የፖለቲካ ድርጅቶችን ያሳተፈ ቢሆንም፣ ሂደቱ የተካሄደው አስቀድሞ በፖለቲካ መሪዎች መካከል ስምምነት ከተደረሰና ትጥቅ የመፍታት ሂደት ከተጀመረ በኋላ ነበር።

በተመሳሳይ እ.ኤ.አ በ2016 በኮሎምቢያ የመንግሥት እና የኤፍ.ኤ.አር.ሲ (FARC) አማፅያን የሰላም ውይይት የተካሄደው በሁለቱ ወገኖች መካከል ለዓመታት የዘለቀ የሰላም ድርድር ከተደረገና ትጥቅ የመፍታት ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው። በየመንና በሱዳን የተካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮችም የፖለቲካ ኃይሎችንና የተለያዩ ወገኖችን ለማቀራረብ ቢሞክሩም፣ ግልጽ የሆነ የህግና የደኅንነት ዋስትና ባለመኖሩ የታጠቁ አካላት አጀንዳቸውን በነፃነት እንዲያቀርቡ የሚያስችል ምሁራዊና ህጋዊ አደረጃጀት አልነበራቸውም።

በእነዚህና በሌሎች ሀገራት የታዩት ተሞክሮዎች የሚያስረዱት ዋና እውነት፣ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በምክክር ሂደት እንዲሳተፉ የሚደረገው ትጥቅ ከፈቱ፣ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ ወይም ተኩስ ካቆሙ በኋላ ብቻ እንደነበር ነው።

በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ሀገራዊ ምክክር ከነባሮቹ ዓለም አቀፍ ልምዶች ፍጹም የተለየና በታሪክ ያልተመዘገበ አዲስ ምዕራፍ ፈጥሯል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በምክክሩ እንዲሳተፉ ያቀረበው ጥሪና የዘረጋው አሠራር ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ የተከናወነ ነው። ኮሚሽኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አስቀድመው ትጥቅ እንዲፈቱ ወይም እጃቸውን እንዲሰጡ ሳይጠይቅ፣ ሀገራዊ ቀውሱን ከስሩ ለመፍታት የሚያስችላቸውን አጀንዳ እንዲያቀርቡ እድል አመቻችቷል።

በተጨማሪም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሐሳባቸውን፣ ስጋታቸውን እና ጥያቄዎቻቸውን ያለ ምንም ስጋት የሚያቀርቡበትና የተወካዮቻቸውን ደኅንነት የሚያረጋግጥ የህግ ዋስትና በኮሚሽኑ ደረጃ ሰጥቷል። ይህ ደግሞ ሂደቱ የችግሩን መንስኤ እንጂ ምልክቶቹን ብቻ ለመፍታት አለመዘጋጀቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ የኃይል እርምጃ ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንዳልቻለ በመገንዘብ የፖለቲካ እና የርዕዮተ-ዓለም ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሐሳብ የበላይነት ለመፍታት የተደረገ ታላቅ እርምጃ ነው።

ይህ አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተለመደ እና ኢትዮጵያዊ መፍትሔ የመሻት ጥበብን የሚያሳይ በመሆኑ ከፍተኛ ሀገራዊና ስትራቴጂያዊ ፋይዳ አለው። በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የቱንም ያህል የተራራቀና የጸና የሐሳብ ልዩነት ቢኖር፣ የታጠቀውም ሆነ ሰላማዊው አካል ድምፁ የሚሰማበት የጋራ መድረክ መፍጠሩ ሂደቱ ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ቅቡልነት እንዲኖረው ያደርጋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ያለፉትን የቁርሾ፣ የጥልና አለመግባባት ታሪኮች በቃኝ በማለት፣ በበሰለና በሰከነ መንገድ የትኛውንም አይነት ሐሳብ ለማስተናገድ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነትና ልበ-ሙሉነት ያሳያል። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ የራሷን ውስብስብ ችግሮች በራሷ መንገድ ለመፍታት የዘረጋችው ይህ የደኅንነት ዋስትና ሰጥቶ የታጠቁ አካላትን አጀንዳ የማስተናገድ አሠራር፣ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ የሰላም ግንባታና የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች በጎ ተምሳሌት ሆኖ የሚያገለግል ነው።

በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን በሙሉ የደኅንነት ዋስትና አጀንዳቸውን እንዲያቀርቡ ማድረጉ፣ ሀገራችን የገባችበትን የታሪክና የፖለቲካ ምህዳር ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት ያላትን ጽኑ ፍላጎትና ልበ-ሙሉነት ያረጋግጣል። ይህ የተለየ ታሪካዊ ተሞክሮ፣ ኢትዮጵያ በኃይል የበላይነት ላይ የተመሠረተውን ጊዜያዊ መፍትሔ ገፍትራ፣ በሐሳብ የበላይነትና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የጠነከረ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ምሰሶ እየጣለች መሆኗን ማሳያ ነው።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: