ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ቁልፍ የበረራ በሮች አንዱ የሆነውን የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናል ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ፕሮጀክቱ ከዘመናዊ ተርሚናልነትም ባሻገር ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።
ከተማዋ በቅርብ ጊዜያት ካስተናገደቻቸው ፈተናዎች ማግሥት ይህ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መጀመሩ የፅናት፣ የማገገም እና ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ማረጋገጫ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዛሬ የተመረቀው አዲሱ ተርሚናል ሰፊ የአውሮፕላን ማቆሚያዎችን፣ የላቁ መሰረተ ልማቶችን፣ የተስተካከሉ መዳረሻ መንገዶችን እና ዘመናዊ መገልገያዎችን ያካተተ መሆኑን በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።
ይህም የአውሮፕላን ማረፊያውን የመቀበል አቅም በማሳደግ የአካባቢውን እያደገ የመጣ ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን፣ ለመንገደኞችም ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ይህ አዲስ ተርሚናል ከተማዋን እያደሰ ካለው የከተማ ትራንስፎርሜሽን ጋር ተዳምሮ ባሕር ዳርን ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ በረራዎች ቁልፍ መዳረሻና ማዕከል እንደሚያደርጋትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመላክተዋል።
አክለውም "ባሕር ዳርን የመሰለች ንቁ ከተማ የምታስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን መጠበቁን እንደሚቀጥል ተስፋ አለኝ" በለዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: