የክረምት ወቅት ለአብዛኞቻችን የእረፍት፣ የመዝናኛ እና ከወትሮው የትምህርት ወይም የሥራ ውጥረት አረፍ የምንልበት ጊዜ ነው። ነገር ግን ይህን ረጅም ጊዜ እንዲሁ በከንቱ ከማሳለፍ ይልቅ፣ የራሳችንን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊለውጥና የሀገራችንን የዲጂታል ሽግግር ሊያፋጥን የሚችል ትልቅ እርምጃ ለመውሰድ ብንጠቀምበትስ?
በአሁኑ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ የዲጂታል ክህሎት የዓለማችን ጠንካራ የኢኮኖሚና የእውቀት መሳርያ ሆኗል። ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ እያደረገችው ያለው “ዲጂታል ኢትዮጵያ” ራዕይም የሚረጋገጠው በቴክኖሎጂ የዳበረና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ሲፈጠር ብቻ ነው።
ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ መነሻ በማድረግ የቀረበው የ“5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች” የነፃ ስልጠና መርሐ ግብር፣ የሀገራችን ወጣቶች የነገዋን ዓለም በዲጂታል እውቀት እንዲመሩና በሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ የተከፈተ ታላቅ የታሪክ እድል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ወጣቶች በዚህ የክረምት ወቅት በነጻ በቀረበው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ የሥልጠና መርሐ ግብር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህም ክረምቱ በከንቱ እንዲያልፍ ሊፈቀድለት እንደማይገባና የሀገራችንን ዲጂታል መፃኢ እድል የሚወስን ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ያሳያል።
ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ ነፃና ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይከፍሉ፣ በቤትዎ ወይም ባሉበት ቦታ ሆነው በራስዎ የጊዜ ሰሌዳና ፍላጎት መከታተል የሚችሉት ሲሆን፣ ዘመናዊና ተፈላጊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ ነው።
በትምህርቶቹም መሠረታዊ ዳታ ሳይንስ (Data Science Fundamentals)፣ መሠረታዊ ፕሮግራሚንግ (Programming Fundamentals)፣ መሠረታዊ አርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ (Artificial Intelligence Fundamentals) ፣ መሠረታዊ አንድሮይድ ኮትሊን ዴቬሎፐር (Android Kotlin Developer Fundamentals) ያሉ ወሳኝ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ተካተዋል።
ሥልጠናውን ሲያጠናቅቁ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና የሥራ ዕድልን ለማግኘት ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የምስክር ወረቀት ይረከባሉ። ይህም በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ያደርግዎታል።
ጊዜ አንዴ ካለፈ አይመለስም። ይህ የክረምት ወቅት ለእርስዎ አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት፣ ራስዎን በዘመኑ እውቀት የሚያበቁበት እና ለወደፊት ሕይወትዎ እንዲሁም ለሀገርዎ የዲጂታል እድገት ጠንካራ መሠረት የሚጥሉበት አጋጣሚ ነው።
ስልክዎን ወይም ኮምፒውተርዎን ተጠቅመው በቀላሉ በመመዝገብ፣ ይህንን ነፃና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ዛሬውኑ መከታተል ይጀምሩ።
የነገ ስኬትዎ የሚጀምረው ከዛሬ ውሳኔዎ ነው። አሁኑኑ ይመዝገቡ፣ ይማሩ፣ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀትዎን ይቀበሉ። የዲጂታል ኢትዮጵያን የወደፊት ጉዞ አብረን እንገንባ!
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: