ታዋቂው የህንድ ሚዲያ 'ፈርስት ፖስት' (Firstpost) በቅርቡ ባወጣው ሰፋ ያለ የቴሌቪዥን ዘገባ፣ የሰው ልጅ ስልጣኔ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የአፍሪካ ቀንድን የኢኮኖሚ ካርታ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀይር በሚችል ግዙፍ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ውስጥ መሆኗን አስታውቋል።
ሚዲያው እንዳስነበበው፣ ኢትዮጵያ ትኩረቷን ከባህላዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በማስፋት በኃይል አቅርቦት፣ በአቪዬሽን፣ በማዕድን፣ በግብርና እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታሪካዊ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ትገኛለች።
ፈርስት ፖስት በዘገባው እንዳብራራው፣ የዚህ ግዙፍ ትራንስፎርሜሽን ዋነኛ ማዕከል የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ ከዓለም ባንክም ሆነ ከአይኤምኤፍ ምንም አይነት ብድር ሳይጠየቅ በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አቅም ብቻ መገንባቱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነፃነት እና ራስን የመቻል ትልቅ ማሳያ ነው ብሎታል።
ይህ ግድብ ንጹህ ኃይልን ለጎረቤት ሀገራት በማቅረብ ቀጠናውን እያስተሳሰረ መሆኑንም ሚዲያው አክሎ ገልጿል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ እየገነባ ያለውና በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው አዲሱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት፣ አዲስ አበባን አፍሪካን ከዓለም ጋር የምታገናኝ ዋነኛ በር፣ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆን ያላትን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ፈርስት ፖስት በዘገባው አትቷል።
እንደ ህንዱ ሚዲያ ፈርስት ፖስት ዘገባ ከሆነ፣ ማዕድን በተለይም የወርቅ ምርት የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ በግብርናው ዘርፍም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በዲጂታል ክህሎት ስልጠና እያገኙና የ5ጂ ኔትወርክ እየተስፋፋ መሆኑን፣ እንዲሁም የካፒታል ገበያ ይፋ መደረጉን ሚዲያው ጠቅሷል።
የዋጋ ግሽበት፣ የዕዳ ሽግሽግ፣ ቀጠናዊ የጸጥታ ፈተናዎች እና የቀይ ባህር ውጥረት ቢኖሩም፣ የብሪክስ (BRICS) አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን፣ ከዓለም ባንክ እና ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ በመቀጠል እያደረገች ያለው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ለውጥ የራሷን ብሎም የቀጠናውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀይር ታላቅ እርምጃ መሆኑን ፈርስት ፖስት በአድናቆት ዘግቧል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: