Search

የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ፣ ለግዛት አንድነት መጠበቅ፣ ለዘመናዊ ቢሮክራሲ ምሥረታ የማይተካ ሚና ተጫውቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ነሐሴ 02, 2018 136

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከኦቢኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ፣ ለግዛት አንድነት መጠበቅ፣ ለዘመናዊ ቢሮክራሲ ምሥረታ እና ለፖለቲካዊ ንቃት ያበረከተውን የማይተካ ሚና በዝርዝር አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ የሚፈልግ አካል ሁሉ ይህንን የማዕዘን ድንጋይ ማፍረስ ሳይሆን መንከባከብ እና መጠበቅ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

 የአሁኗን ኢትዮጵያ ድንበር በማስፋት እና በማስከበር ረገድ እንደ ራስ ጎበና ዳጬ ያሉ የኦሮሞ ጀግኖች ትልቅ ሚና እንደነበራቸው አንሥተዋል።

 ታሪካዊ ሰዎችን በዛሬው መነጽር መተቸት እና ጉድለታቸውን ብቻ በማጉላት ታሪካቸውን ማሳነስ ተገቢ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። ይህንንም በምሳሌ ሲያብራሩበዘመኑ ከነበሩ መሪዎች አሁን ያለውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዕውቀት እንደመጠበቅነው ብለዋል።

በሉዓላዊነት እና በጦር ሜዳ የተከፈለ መስዋዕትነት

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት እንዳትወድቅ በደም እና በአጥንት ከተከላከሉት ጀግኖች መካከል የኦሮሞ ልጆች ግንባር ቀደሞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዓድዋን፣ ማይጨውን፣ ካራማራን እና ባድመን በምሳሌነት በማንሣት፤ የፊት አውራሪ ገበየሁ፣ የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ የደጅአዝማች ገረሱ ዱኪ፣ የኮሎኔል አብዲሳ አጋ፣ የጄኔራል ጃጋማ ኬሎ እና የጄኔራል ታደሰ ብሩን ጀግንነት በታሪካዊ ማሳያነት አቅርበዋል።

በዘመናዊ ቢሮክራሲ፣ ጦር እና የተማሪዎች እንቅስቃሴ የነበረው ድርሻ

የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፋይናንስ ቢሮክራሲ በመገንባት የዴሬሳ ልጆች የነበራቸውን ከፍተኛ ሚና፤ በዘመናዊ ጦር የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት በማዘመን ረገድ የጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊን ጉልህ አስተዋጽኦ፤ "መሬት ላራሹ" የሚለውን ጥያቄ በማንገብ በተደረገው የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች (እንደ ኢህአፓ እና መኢሶን ያሉ) ምሥረታ ላይ እነ ኃይሌ ፊዳ እና ባሮ ቱምሳ የነበራቸውን ሰፊ ፖለቲካዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ አመራር አብራርተዋል።

ይህችን ሀገር አባቶቻችን በደማቸው እና በልፋታቸው ገንብተዋታል፤ ያቺን ሀገር አሁን ልንጥላት አይገባም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በታሪክ ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን አርሞ እና ተምሮ ማለፍ እንጂ፣ የተሠራውን ገድል መካድ፣ ማሳነስ እና ታሪክን መቅበር ለትውልድ እንደማይጠቅም ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዮናስ በድሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: