መንግሥት ባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ሲሰራው የነበረው ሪፎርም የሕግ አስከባሪ አካላት በሰው ኃይል፣ በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ዘመናዊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
የዚህ የለውጥ ጉዞ ማሳያ የሆነው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሕዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም የተመረቀው የፎረንሲክ ምርመራ እና የምርምር ልህቀት ማዕከል፣ የሀገራችንን የፍትህ ስርዓት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው።
ከዚህ ቀደም ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የፎረንሲክ ዘረመል (DNA) ላብራቶሪ፣ የወንጀል ምርመራ ሥራን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ነፃ በሆነ መልኩ አስተማማኝ የቴክኒክ ማስረጃዎችን በማቅረብ እያከናወነ ይገኛል።
ማዕከሉ በማስረጃ እጥረት ተድበስብሰው ይቀሩ የነበሩ ውስብስብ የወንጀል ድርጊቶችን በሳይንሳዊ መንገድ በማጣራት ጥፋተኞችን ለፍርድ በማቅረብና ንጹሃንን ነፃ በማውጣት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ ይህም ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ትልቅ እውቅናን አትርፎለታል።
የማዕከሉ አደረጃጀት ዘርፈ ብዙ እና እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የላብራቶሪ ክፍሎች የተዋቀረ ነው። የባዮ-ኬሚስትሪ ላብራቶሪው የዲ.ኤን.ኤ (DNA) እና የተለያዩ የሰውነት ናሙናዎችን ትንተና በማካሄድ የሰውን ማንነት እና የዝምድና ግንኙነት በአስተማማኝ ሁኔታ ያረጋግጣል።
የቃጠሎና ፍንዳታ ምርመራ ክፍሉ በበኩሉ የጥፋት ምልክቶች በሚታዩባቸው ቦታዎች በአካል በመገኘት የቃጠሎ መነሻ ነጥቦችንና የፍንዳታ መንስኤዎችን በመለየት መረጃዎችን ወደ ጠቃሚ ማስረጃነት ይቀይራል።
በተመሳሳይ የዲጂታል ፎረንሲክ ክፍሉ ኮምፒውተሮችን፣ የሞባይል ስልኮችን፣ ሲም ካርዶችን፣ የሲሲቲቪ ካሜራዎችን እና የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን በጥንቃቄ በመመርመር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በማጋለጥ የኢንፎርሜሽን ዘመን ፈተናዎችን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።
የአካላዊ ፎረንሲክ ዘርፍ ደግሞ የሰነድ ምርመራዎችን፣ የጦር መሳሪያ ምርመራዎችን እንዲሁም የተለያዩ ፈለጎችን እና የመኪና ሞተር ቁጥሮችን በመለየት ረቂቅ የሆኑ ማስረጃዎችን ለፍትህ ሂደት ያቀርባል።
የአሻራና ወንጀል ሪከርድ ምርመራ ክፍሉም የተጠርጣሪዎችን የ10 ጣት አሻራ ከመመዝገብ አልፎ ማህደር መክፈት፣ ነፃ ማውጣት እና ከኢንተርፖል የሚመጡ አሻራዎችን ተቀብሎ በመመርመር የሕግ ስርዓቱን እያጠናከረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፍትህ ሥርዓቱን በሳይንሳዊ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ለማድረግ የጀመረው ይህ ታሪካዊ ጉዞ፣ ከለውጡ በፊት የDNA ናሙናዎችን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ችሏል።
ዛሬ ላይ የላብራቶሪው አቅም ከሀገር አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት በመስጠት ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማድረግና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች፣ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት እና ለአፍሪካ ምሳሌ የሆነች ሀገርን ለማስረከብ ታሪክ እየጻፈ ይገኛል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: