ኢትዮጵያ አንድን ታላቅ ሀገራዊ የልማት ስራ ስትጀምር ሁልጊዜም በጭብጨባ፣ በድጋፍ እና "በርቺ" በሚል አበረታች ቃል ታጅባ አይደለም። ይልቁንም፣ "እንዴት ይህን ይጀምራሉ? ምን ሊያደርግላቸው ነው? ይህ እኮ የቅንጦት ልማት ነው!" በሚሉ አፍራሽ ቅጥያዎች እና ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ በሚስተጋቡ ተስፋ አስቆራጭ ጩኸቶች መታጀብ የተለመደ እጣ-ፈንታዋ ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የውስጡን ተጠራጣሪ ስራው ሲያልቅ እንደሚሳሳት እና እንደሚያምን በማወቅ፣ ለውጭው ዓለም ደግሞ በማስረዳትና በተግባር በማሳየት ያሰበችውን ከመፈጸም ወደኋላ ብላ አታውቅም።
በዚህም በልማት ጉዞዋ በሚያጋጥሟት ፈተናዎች ሁሉ ውስጥ አልፋ ሁሌም የመጨረሻውን ሳቅ ትስቃለች።
ለዚህ እውነታ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዞ ህያው ምስክር ነው። ፕሮጀክቱ ሲበሰር ጀምሮ የነበሩት ጩኸቶች፣ "አይችሉም፣ አቅም የላቸውም፣ አይጨርሱትም" ከሚሉ ትርክቶች ተነስተው በተለያየ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲታጀቡ እንደነበር ለሁሉም ግልጽ ነው።
ኢትዮጵያ ግን እያደገ የሚሄድ እና የሚያሳምን ስራዋን ከቃል በላይ አሳድጋ፣ የዓለምን ጫና ተቋቁማ በተግባር እያሳየች የመጨረሻውን ሳቅ ስቃለች።
የኮሪደር ልማት ሲጀመርም የገጠመው ፈተና ከዚህ የተለየ አልነበረም። የከተማዋን ገጽታ በሚቀይረው በዚህ ስራ ላይ "ምን ያደርጋል?" በሚል ቁንጽል እሳቤ የተነሳ ማጣጣል ቢገጥመውም፣ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ጀምራ በክልል ከተሞችም በማስፋፋት በተግባር አሳይታለች።
ዛሬ ላይ ትችቱ "እንዲህ ከሚያደርጉት እንደዚህ ቢያደርጉት" ወደሚል ገንቢ ሀሳብ ካልተቀየረ በቀር ለነቀፌታ የማይመች ሆኗል። እዚህም ላይ ሀገራችን ብዙ እንቅፋቶችን ብታልፍም ዳግም በድል ሳቀች።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የስንዴ ልማትን በስፋት ስትጀምር፣ ሀሳቡ አላስፈላጊ ስለመሆኑ በብዙ ትንንሽ ትርክቶች የታጀበ ድምጽ ይሰማ ነበር።
እንደውም ከራሳችን አልፈን ለውጭ ገበያ እናቀርባለን የሚለው ከፍ ያለው የሀገር አቋም ሲሰማ፣ "እንዴት?" ብሎ ለመጠየቅ ያልቻለ ብዙ ነበር።
ነገር ግን በፍጹም ተሞክሮ በማያውቅ ቦታ ጭምር በበጋ የተሰራው የስንዴ ልማት፣ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ግዙፍ አምራች ከማድረግ አልፎ እንደቃሏ ለውጭ ገበያም በማቅረብ የመጨረሻውን ሳቋን ከመሳቅ አላገዳትም።
በተመሳሳይ በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥንና በረሃማነትን እንከላከላለን ስትል ማን ሰማት? እሷ ግን በየዓመቱ በአንድ ጀምበር አዳዲስ ሪከርዶችን እያስመዘገበች ዓለምን አስደምማ እቅዷን አሳክታለች።
ዓለም በአየር ንብረት መዛባት ሲሰቃይ፣ ከአፍሪካ ይህ መፍትሄ ይመጣል ብሎ የጠበቀ ባይኖርም፣ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለጎረቤቶቿም በመትረፍ የመቻልን አብነት አሳይታለች።
ከእነዚህ ባሻገር፣ አሁን ላይ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በአቪዬሽን ማስፋፊያ እና በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገች ያለው ግዙፍ ርምጃ ተመሳሳይ ማሳያ ነው።
"በዚህ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ሆነው አዳዲስ ግዙፍ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎችን፣ የማዕድን ማውጫዎችን እና የቴክኖሎጂ ማዕከላትን መገንባት አይችሉም" የሚሉ አካላት ዛሬም አሉ።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማታጠናቅቅበት ታሪክ የላትምና፣ በነዚህም መስኮች የውጭ ጫናዎችን እና የውስጥ ፈተናዎችን በጽናት አልፋ ድሏን እያበሰረች ነው።
አሁን ዓለም ሁሉ ኢትዮጵያ የምትጀምረውን ፕሮጀክት ሁሉ ቀስ ብሎ መመርመር እና ማጤን እንደሚገባው ተረድቶ፣ ከፕሮጀክቶቿ ጎን ለመቆም ፍላጎቱን ማሳየት ጀምሯል።
ይህ ሁሉ ጽናት፣ ይህ ሁሉ የመቻል ምስጢር ስሩ የተቀበረው በታላቁ የዓድዋ ድላችን ውስጥ ነው። ትላንት "ይሸነፋሉ፣ አይችሉም፣ አቅም የላቸውም" ተብለው በዓድዋ ተራሮች ላይ አባቶቻችን የጻፉት ታሪክ፣ በደማቁ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የሚያበራ ህያው የልብ ብርሃን ነው።
ያ የአሸናፊነትና የመቻል መንፈስ ዛሬ ለእያንዳንዱ የልማት ስኬታችን ምልክት ሆኖ ቀጥሏል። ያ የዓድዋ ብርሃን የዛሬው የመቻል ማሳያችን ብቻ ሳይሆን፣ ለነገው ትውልድም ፈተናን የማለፍ ጥበብ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ፈተናዎች ቢበዙ፣ እንቅፋቶች ጎንበስ ቢያደርጉም፣ ከዓድዋ የወረስነው የመቻል አቅም ኢትዮጵያ የመጨረሻውን ሳቅ ከመሳቅ የሚያግዳት ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ያለፉት ዓመታት ህያው ምስክሮች ናቸው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ሁሌም የመጨረሻውን ሳቅ የምትስቀው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: