የሀገርን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የልማት ጉዞ የሚያደናቅፈውን ሌብነትና ብልሹ አሠራር ለመዋጋት መንግሥት እየወሰደ ባለው የተቀናጀ እርምጃ፣ በልዩ ልዩ የመንግሥት ተቋማት እና የግል ዘርፍ ውስጥ የተሸሸጉ አካላት ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሌብነት የኢትዮጵያ ታላላቅ የልማት ግቦች እና የብልጽግና ራዕይ ዋነኛ ማነቆ መሆኑን በመግለጽ፣ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት በጽናት እንደሚሠራ እና በማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይል በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
አሁን ላይ በተደረጉ ጥናቶች እና ምርመራዎች መሰረት፣ በተለይም በዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እና በገቢዎች እና ጉምሩክ ዘርፍ ላይ የታዩ ሕገ-ወጥ አሠራሮች እና የሙስና አሻጥሮች ላይ እርምጃዎች መወሰድ ተጀምሯል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አካባቢ ሕገ-ወጥ ኤጀንሲዎችን በመጠቀም ዜጎች ውል ወደሌላቸው ሀገራት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ፣ ያልተገባ ኮሚሽን መቀበልና በዜጎች ላይ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ እንግልት ማድረስ በተከሰሱ አካላት ላይ የህግ እርምጃ ተወስዷል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሀገርን የገቢ አቅም በሚጎዱ የግብር ስወራ፣ የኮንትሮባንድ ዝውውር እና የጉምሩክ አሠራር ማጭበርበሮች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና ነጋዴዎች ተለይተው በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።
ይህ የተጀመረው አጠቃላይ የመንግሥት ንቅናቄ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን፣ ለሌብነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ብልሹ አሠራሮችን በሥርዓት ለማስወገድ ያለመ ነው።
አሠራሮችን ማዘመን፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታላይዜሽን መደገፍና ግልጽ አሠራርን መዘርጋት የመፍትሔው አካል ተደርጎ በመደመር መንግሥት በመተግበር ላይ ይገኛሉ።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: