በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘንድ ትውልድ ሲሻገር የቆየውና ለዘመናት የሰላም፣ የአብሮነት እንዲሁም የዕርቅ መሠረት ሆኖ ያገለገለው ሀገረሰባዊ የምክክር ሂደት ዛሬም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
ከእነዚህ ውድ ባሀገረሰባዊ እሴቶች መካከል አንዱ የወላይታ ብሔር የዕርቅ ሥርዓት የሆነው "አዋሲያ" ይገኝበታል። "አዋሲያ" በወላይትኛ ቋንቋ የተጣሉ ወዳጆችን፣ ቤተሰቦችንና ጎረቤቶችን የማስታረቅ፣ የማስማማት፣ ፀብ የማብረድና ሰላምን የማስፈን ጥበብ ያለው ጥልቅ ሥርዓት ነው።
በሰዎች መካከል ፀብ፣ ቁርሾ ወይም አለመግባባት ተፈጥሮ የማይጠያየቁና በክፉም ሆነ በደጉ የማይደራረሱ ጎረቤታሞች ወይም ቤተሰቦች ሲኖሩ፣ የችግራቸው መንስኤ በሀገር ሽማግሌዎች ወይም በቅርብ ወዳጆች ይጠየቃል።
ዘመድ አዝማድ ከተጣሉት ጋር በመገናኘት በደል ደርሶብኝ ወይም በድያለሁ የሚለውን እውነታ እንዲያወያዩአቸው ያደርጋሉ።
የተጣሉት በመጀመሪያ ለየብቻቸው ከተጠየቁ በኋላ፣ በአንድ ላይ ተቀምጠው የተፈጠረውን አለመግባባት በግልጽ እንዲያስረዱ የጋራ ቀን ቀጠሮ ይያዝላቸዋል።
የ"አዋሲያ" ቀጠሮ በህብረተሰቡ ዘንድ እጅግ ታላቅ ክብር የሚሰጠው በመሆኑ ቀጠሮውን ማክበር እና አለመቅረት ግዴታ ነው።
ዕርቁን የያዙት ሽማግሌዎችም በመጀመሪያ ከሁሉ አስቀድመው በመካከላቸው ፈጣሪ ሰላሙን እንዲያወርድ በጸሎት ሥርዓቱን ይጀምራሉ።
በመቀጠልም ከተጣሉት መካከል በዕድሜ ከታላቁ ግለሰብ ወይም ቅድሚያ ከሚገባው ጀምሮ ስለተፈጠረው ቁርሾ ሰፊ ማብራሪያ ይደመጣል።
ሽማግሌዎቹ የሁለቱንም ወገን ሀሳብ በጽሞና ካደመጡ በኋላ "አንተም ይሄን ተው፣ አንተም ይሄን ተው፤ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ አያዋጣም" በማለት ወደሚያስማማና የጋራ ወደሚያደርግ ሀሳብ ያመጣሉ።
ይህ የሽማግሌዎች ወይም የሃይማኖት አባቶች የጋራ ሀሳብም በተከራካሪዎች ዘንድ በሙሉ ክብር ተቀባይነትን ያገኛል።
በ"አዋሲያ" ሥርዓት ጣት የመቀሳሰር ወይም የጥፋተኝነት ፍረጃ ቦታ የለውም፤ ይልቁንም "ይቅር ለእግዚአብሔር" ተብሎ ከልብ የመነጨ ይቅርታ ይወርዳል።
ይህ የምክክር ሂደት በቤተሰብ፣ በወዳጅና በዘመድ ዘንድ እያደገ ሊሄድ የሚችለውን ደም መፋሰስ፣ የቤተሰብ መበታተንና አለመረጋጋትን ከመሰረቱ የሚያስቀር በመሆኑ በብሔሩ ዘንድ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።
ሥርዓቱ ያለፈውን ቁርሾ ሳይሆን ወደፊት አብሮ መኖርን የሚያስቀድም፣ ከቅጣት ይልቅ ሁለቱም አሸናፊ የሚሆኑበት ፍትሃዊ ዕርቅ ነው።
የግለሰቦች የጥል መንስኤ ለውጭ አካል ሳይወጣ በአስታራቂዎች ብቻ ሚስጥሩ ተጠብቆ የሚፈታ በመሆኑ፣ ሰዎች ከውስጣቸው አውጥተው ተነጋግረው ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑ ያደርጋል።
በዘመናዊ የፍርድ ሂደት የሚወሰደውን የጊዜ እና የገንዘብ ወጪ፣ እንዲሁም በአጥፊው አካል ላይ የሚፈረደውን ቅጣት በማስቀረት አብሮነትን በጽኑ አለት ላይ ያትማል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክርና የሰላም ጥረቶችን እያደረገች ባለችበት በዚህ ወሳኝ ጊዜ፣ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ ያሉትን እንደ "አዋሲያ" ያሉ ሀገረሰባዊ የዕርቅና የመመካከር ልምዶች አጠናክሮ ማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነው።
እነዚህን ውድ ማህበራዊ እሴቶች በአግባቡ በመያዝ፣ ከዘመኑ ጋር እያዋሃዱ ሳይበረዙ ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር የሁላችንም ትውልዳዊ ኃላፊነት ነው።
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: