Search

ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል የተሻገረው የኢትዮጵያ የጤና ጉዞ

ቅዳሜ ነሐሴ 02, 2018 142

የአንድ ሀገር የልማት ስኬት የሚለካው በመንገዶችና በሕንፃዎች ብቻ ሳይሆን በዜጎች ጤና፣ በሕክምና ተደራሽነት እና ዜጎች በችግር ጊዜ በሀገራቸው ውስጥ የሚያገኙት የሕክምና አቅምም ጭምር ነው።

በዚህ መስፈርት ሲታይ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የተጀመሩ ለውጦች ከተለመደው የጤና አገልግሎት ማስፋፋት በላይ የሚሄዱ ናቸው።

ይህ ለውጥ አንድ ትልቅ ጥያቄን ይመልሳል፤ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የሚያስፈልገውን የጤና አገልግሎት በራሷ አቅም ምን ያህል ማቅረብ ትችላለች? የጤና ልማቱ አንዱ ግልጽ መገለጫ የጤና ተቋማትን አቅም ማሳደግ ነው።

አዳዲስ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ ያሉትን ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በላቀ ምርመራ መሳሪያዎችና በልዩ ሕክምና አቅም ማስፋፋት የለውጡ አካል ሆኗል።

ይህም ከተለመደው ታካሚው ሕክምና ለማግኘት ወደ ውጭ መሄድ አለበት ከሚለው አስተሳሰብ ወደ ዘመናዊ ሕክምናን በሀገር ውስጥ ማግኘት የለወጠ ነው። በተለይ በላብራቶሪ ምርመራ ዘርፍ የተጀመረው ለውጥ የጤና ሉዓላዊነት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያሳያል።

በቀድሞው አሠራር በሀገር ውስጥ በቂ የምርመራ አቅም ባለመኖሩ ሕይወትን ሊያሰጉ የሚችሉ የበሽታ ናሙናዎች ወደ ውጭ አገራት ይላኩ ነበር። ይህ የገንዘብ ወጪን ብቻ ሳይሆን የምርመራ ውጤት እስኪመጣ የሚወስደው ጊዜ የታካሚውን ሕክምና ያዘገያል።

ዛሬ ግን በሀገር ውስጥ የላቀ የላብራቶሪ አቅም በመገንባት ይህንን አሰራር በመቀየር ላይ ነው።

በአለርት የተገነባው ዘመናዊ ላብራቶሪም በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ ምሳሌዎች አንዱ ነው።

የጤና ሉዓላዊነት በሆስፒታልና በላብራቶሪ ብቻ አይጠናቀቅም በዚህም መድኃኒት የጤና ሥርዓቱ ዋነኛ መሠረት ነው። አንድ ሀገር ሆስፒታል ቢገነባ፣ ዘመናዊ ማሽኖችን ብታሟላ ነገር ግን መድኃኒትን በተረጋጋ ሁኔታ ማቅረብ ካልቻለች የጤና ራስን መቻል ሙሉ አይሆንም።

ስለዚህ የመድኃኒት ምርትን በሀገር ውስጥ ማሳደግ በመድኃኒት አቅርቦት ራስን ለመቻል የሚደረገው ጉዞ የጤና ልማቱ ዋነኛ አጀንዳ ነው።

በላብራቶሪዎችና በጤና ተቋማት መካከል የዲጂታል መረጃ ልውውጥ ማሳደግ የምርመራ ጊዜን ለማሳጠር፣ የታካሚ መረጃን በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደርና የጤና ውሳኔዎችን በመረጃ ላይ ለመመስረት ያግዛል።

ስለሆነም ከአንድ የጤና ተቋም የተነሳ ናሙና ወይም መረጃ በፍጥነት ወደ ልዩ ምርመራ ማዕከል ሊደርስ እና ውጤቱም በዲጂታል ሥርዓት ወደ ሕክምና ቦታው ሊመለስ ከቻለ ቴክኖሎጂው በቀጥታ የሰው ሕይወትን የሚያገለግል መሣሪያ ይሆናል።

አንድ ድሃ ዜጋ ውድ የሆነ የምርመራ ወጪ መሸፈን ሳይችል ሕክምናው እንዳይዘገይ፣ አንድ ታካሚ ውጤቱን ለሳምንታት ሳይጠብቅ፣ ቤተሰብ የሚወደውን ሰው ለሕክምና ወደ ሩቅ አገር ለመላክ እንዳይገደድ ይህ የጤናው ዘርፍ የታየው ልማት ትክክለኛ ትርጉም አለው።

ባለፉት የለውጡ ዓመታት የተጀመሩት የጤና ዘርፍ ለውጦች እንደ አንድ የተናጠል ፕሮጀክት ሳይሆን እንደ አንድ ትልቅ ራዕይ ሊታዩ ይገባል።

የናሙና ስደትን ማብቃት፣ የውጭ ሕክምና ጥገኝነትን መቀነስ፣ የመድኃኒት ምርትን ማሳደግ እና የዘመናዊ ምርመራ አቅምን በሀገር ውስጥ ማስፋፋት እነዚህ ሁሉ በአንድ ላይ ሲታዩ የሚገኘው ውጤት የጤና ሉዓላዊነት ነው።

ኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቷን ከማስፋፋት ወደ ማዘመን ከዘመን ወደ ራስን መቻል እየተሻገረች ነው።

ይህ ጉዞ ገና የተጠናቀቀ ባይሆንም አቅጣጫው ግን ግልጽ ነው ጤና በገበያ የሚገዛ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነት መሠረት መሆኑን ያሳየ ነው

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: