በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካ ትንታኔ መሠረት፣ የባሕር በር ከንግድ ማስተላለፊያነት ባለፈ የብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ የደህንነት እና የጂኦ-ስትራቴጂካዊ የበላይነት ቁልፍ መሠረት ሆኗል።
ዛሬ ላይ የዓለም ኃያላን አገራት የፖለቲካ ጡንቻ እና የተፅዕኖ አቅም የሚለካው፣ የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነታቸውን በማስጠበቅ እና ስትራቴጂካዊ የባሕር ላይ ንግድ መስመሮችን በመቆጣጠር ረገድ ባላቸው ኃይል ነው።
ወደብ የሌላት አገር የሎጂስቲክስ ነፃነቷ በከፍተኛ ደረጃ የተገደበ በመሆኑ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነቷ ሁልጊዜም ቢሆን በጎረቤቶቿ በጎ ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ብሔራዊ ደህንነትን በቀላሉ አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት ነው።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ስንቃኝ፣ ሰፊ የባሕር በር ባለቤትነት ለኃያላኑ አገራት የሉዓላዊነት ክብር እና የኃይል ማሳያ ሆኖ እናገኘዋለን።
ለአብነት ያህል አሜሪካን ብንወስድ፣ የዓለምን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሥርዓት የምትዘውረው በሁለቱ ውቅያኖሶች ማለትም በአትላንቲክና በፓሲፊክ ላይ ባላት ሰፊ የባሕር ዳርቻ እና እንደ ሎስ አንጀለስ፣ ሎንግ ቢች በመሳሰሉት ግዙፍ ወደቦቿ አማካኝነት ነው።
አሜሪካ ዘመናዊ የባሕር ኃይሏን (Blue-water Navy) በመጠቀም የራሷን የሎጂስቲክስ መስመር ከማስጠበቅ እና የሺፒንግ መስተጓጎልን ከመከላከል አልፋ፣ በሌሎች አገራት ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የመጣልና የንግድ እገዳ የማድረግ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተፅዕኖ መፍጠር ችላለች።
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ቻይና የዓለም ሁለተኛዋ የኢኮኖሚ ሞተር ለመሆን የቻለችው በሻንጋይ፣ ሼንዘንና ኒንግቦ በመሳሰሉት ግዙፍ ወደቦቿ አማካኝነት አምራች ኢንዱስትሪዎቿን ከዓለም ገበያ ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር ነው።
ከዚህም ባለፈ ቻይና የውጭ ኃይሎች በሎጂስቲክስ መስመሯ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ማነቆ ለመከላከል "የዕንቁዎች ድርድር" (String of Pearls) በተሰኘው ጥልቅ የደህንነት ስትራቴጂዋ በህንድ ውቅያኖስና በቀይ ባሕር አካባቢ ወደቦችን መገንባትና የባሕር ኃይል ሠፈሮችን ማቋቋም ችላለች።
ይህ ተግባር የወደብ ባለቤትነት እና የባሕር መስመር ደህንነት ለዘመናዊ ሉዓላዊነትና ለኢኮኖሚ ማስፋፋት ያለውን ወሳኝነት በግልፅ የሚያሳይ ሕያው ዳታ ነው።
ወደብ ያላቸው አገራት በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ የራሳቸውን የንግድ መርከቦች በማንቀሳቀስ፣ የገቢና ወጪ ንግዶቻቸውን ከማንኛውም ጂኦ-ፖለቲካዊ መስተጓጎል ይታደጋሉ። ይህ "የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነት" የውጭ ኃይሎች በውስጥ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ጫና እንዳያሳድሩ እንደ ትልቅ የብሔራዊ ደህንነት ጋሻ ያገለግላል።
የባሕር በር ማጣት ግን አገራትን ለጂኦ-ፖለቲካዊ መታገቻነት በማጋለጥ ለውጭ ፖለቲካዊ ጫና በቀላሉ እንዲንበረከኩ ያደርጋቸዋል።
ይህንን ዓለም አቀፋዊ ሐቅ ይዘን ወደ አገራችን ስንመጣ፣ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን አንገብጋቢ የህልውና ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በአፍሪካ ቀንድ እጅግ ስትራቴጂካዊ በሆነ ቀጠና የምትገኝና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ያለች አገር፣ የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነቷ በሌሎች አገራት ወደቦች ላይ መቶ በመቶ ጥገኛ መሆኑ ታላቅ የደህንነት ስጋት ነው።
በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ትንታኔዎች እንደሚያሳዩት፣ የኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነው የገቢና ወጪ ንግድ በአንድ የወደብ መስመር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑ፣ አገሪቱን ለማንኛውም የውጭ ፖለቲካዊ ጫና እና የሎጂስቲክስ መቆራረጥ እጅግ ተጋላጭ ያደርጋታል።
ለወደብ ኪራይና ለትራንዚት በየዓመቱ የሚወጣው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚፈታተን ማነቆ ነው።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሙሉ እና የማይደፈር የሚሆነው፣ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸውን ቁልፍ ሸቀጦች (ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒትና የጦር መሣሪያዎችን ጨምሮ) እንዲሁም ወደ ውጭ የምትልካቸውን የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርቶች ያለ ምንም የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት፣ ክልከላና የፖለቲካ ጫና ማስተላለፍ ስትችል ብቻ ነው።
የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ነፃነቷን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የቀጠናውን የኃይል ሚዛን እንድታስጠብቅ፣ የባሕር ኃይሏን መልሳ በማቋቋም ብሔራዊ ደህንነቷን ከውጭ ትንኮሳ እንድትከላከል እና የዓለም አቀፍ ንግድ ተወዳዳሪነቷን እንድታሳድግ ያስችላታል።
በዛሬው እጅግ ተለዋዋጭና ፉክክር በበዛበት የዓለም የጂኦ-ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ፣ እውነተኛ ሉዓላዊነት ማለት ድንበርን በጦር መሣሪያ ከመጠበቅ ባሻገር ዘላቂ የኢኮኖሚና የሎጂስቲክስ ነፃነትን በተግባር ማረጋገጥ ማለት ነው።
አሜሪካ፣ ቻይና እና ሌሎችም በኢኮኖሚ የበለፀጉ አገራት በሰፊ የባሕር በሮቻቸው አማካኝነት የሉዓላዊነት ክብራቸውን፣ የንግድ መስመራቸውንና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን እንዳስጠበቁት ሁሉ፤ ኢትዮጵያም ዘላቂ ብሔራዊ ሉዓላዊነቷን፣ የደህንነት ዋስትናዋን እና ታሪካዊ የጂኦ-ፖለቲካ ክብሯን ለማስቀጠል የራሷ የሆነ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ ታሪካዊ፣ ሞራላዊና ፖለቲካዊ ግዴታ ነው። ይህ እውን ሲሆን ብቻ የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነቷ ይረጋገጣል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: