በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መሠረታዊ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ይህ ታሪካዊ መድረክ በሂደቱ የሚስተዋሉ የሐሳብ ፍጭቶችና ክርክሮች የምክክሩን እውነተኛነትና ዴሞክራሲያዊነት የሚያሳዩ ሲሆን፣ ቅሬታዎችና ልዩነቶች ሳይሸሸጉና ሳይድበሰበሱ አደባባይ ወጥተው በሐሳብ መሞገታቸውና አሳማኝ መፍትሔ መፈለጉ ለዘላቂ ሰላም መሠረት ነው።
በሀገራችን የረጅም ዓመታት የሰላምና አንድነት ጉዞ ላይ ታሪካዊ ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን በመደቀን የምክክሩን ሂደት ጥላሸት ለመቀባትና የሐሰተኛ መረጃ መርዞችን ለመርጨት የሚጥሩ አካላትን በንቃት መከላከል ይገባል።
የኢትዮጵያ የእርቅና የሽምግልና ሥርዓቶች ትናንት ተጀምረው ዛሬ የሚያልቁ ጊዜያዊ ክስተቶች ሳይሆኑ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ የመጡ የኅልውና መሠረቶች ናቸው።
ትናንት በየአካባቢው በዛፎች ጥላ ሥርና በወንዞች ዳርቻ ይደረጉ የነበሩ እውነትንና ፍጹም መከባበርን መሠረት ያደረጉ ባህላዊ የእርቅ እሴቶች ዛሬ አድገውና ሰፍተው ወደ ሀገር አቀፍ የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር ተሸጋግረዋል።
ይህ ርምጃ የትናንቱን ባህላዊ ጥበብ ከዘመናዊው የፖለቲካና ማኅበራዊ ውይይት ጋር በማስተሳሰር "መነጋገር ከጥል ያድናል" የሚለውን አባባል በተግባር እየገለጸ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተመረጡ ፖለቲከኞች፣ መምህራን፣ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ሴቶችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጉባኤው ላይ በንቃት በመሳተፍ የጋራ መግባቢያ ነጥቦችን በመፈለግ ላይ ናቸው።
ተመካካሪዎቹ በባለሙያዎች የሚሰጡ ሳይንሳዊ ማብራሪያዎችን እያገኙ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መልኩ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እየፈቱ ይገኛሉ። በዚህ የታሪካዊ ሂደት ውስጥ የሚፀድቁት ቃለ ጉባዔዎችና የሚደረሱባቸው የመግባቢያ ሐሳቦች ለወደፊቱ የሀገራችን መዋቅራዊ ለውጦችና ለሰላም ግንባታ ሥራዎች እንደ ዋና ግብአት ያገለግላሉ።
የመደማመጥ፣ የመቻቻል እና የመደራደር ባህል ከተግባራዊ ቁርጠኝነት ጋር ሲዋሃድ ይህ ታሪካዊ ምክክር ከቃላት ባለፈ በዜጎች መካከል የመተማመን መንፈስን በመፍጠር ለነገዋ ኢትዮጵያ የማዕዘን ድንጋይ የሚሆን ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: