ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፖለቲካው እና በማኅበራዊው ዘርፍ የሚታዩ ልዩነቶችን ለመፍታት የሀገራዊ ውይይት፣ የሕግ የበላይነት እና የሰላም መንገድ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ወጥተው ድምፃቸውን መስጠታቸው ትልቅ ፖለቲካዊ መልዕክት አለው።
ከ51 ሺህ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች 54 ሚሊዮን ሕዝብ ወጥቶ መምረጡ፣ ሥልጣንን በኃይል የመያዝ እኩይ አካሄድ ቦታ ሊኖረው እንደማይገባ ለወዳጅም ሆነ ለጠላት በተግባር ያሳየ ዴሞክራሲያዊ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ ድምጽ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ በመሆኑ ለመንግሥት ልዩ የኃላፊነት ስሜት እንደሚፈጥርም አክለዋል።
የሕዝቡን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር እና ሀገርን ወደፊት ለመውሰድ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት፣ የጋራ ስትራቴጂካዊ ግብ ማሰናዳት፣ አንድነትን መጠበቅና የተገኘውን ሀብት እና ስኬት እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ተከማችተው የቆዩ ሀገራዊ ችግሮች በአንድ ወገን ውሳኔ ብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ፣ አሁን እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ይህ ሲሆንም አሳታፊ በሆነ መንገድ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላም እና ፈጣን ልማት ማምጣት እንደሚቻል አስረድተዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የምግብ ዋስትናን ሙሉ በሙሉ በማረጋገጥ የምግብ ጉዳይ አጀንዳ እንዳይሆን በትኩረት እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ከዚህም ባሻገር ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት ጥሎ ሲመርጥ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጠው እና ሌብነት እንዲጠፋ መፈለጉን ጠቁመው፣ ይህንንም ለማሳካት ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም ቢሮክራሲን እና ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ ጠንካራ ሥራ እንደሚሠራ አብራርተዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: