የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ከሚባሉና በርካታ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን ከሚያስገኙ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት፣ በታሪክ፣ በባህልና በቅርስ ብዝኃነት ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ቀደምት ስም ካላቸው ሀገራት አንዷ ብትሆንም፣ ዘርፉ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለኢኮኖሚው ያበረከተው አስተዋጽዖ ካላት እምቅ አቅም ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ እንደነበር ይታወቃል።
ነገር ግን በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዘርፉ በተደረጉ ሀገራዊ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የታደሱ የመስህብ ስፍራዎች ምክንያት የቱሪዝም ዘርፍ እንደገና በማንሰራራት የሀገራችንን የኢኮኖሚ ምሰሶነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ የቱሪዝም ዘርፍ ትልቁ አስተዋጽዖ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በኩል ያለው ሚና ነው። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የሚያወጡት ወጪ በሸቀጣ ሸቀጥ ኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ በመተካት የሀገራችንን የንግድ ሚዛን ያስተካክላል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማት እንዲሁም የሆቴልና የትራንስፖርት ዘርፎች ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሪ ማሰባሰቢያ መንገዶች በመሆን ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ቱሪዝም ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ዘርፍ በመሆኑ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።
በሆቴሎች፣ በኤጀንሲዎች፣ በጉብኝት መሪዎች እና በትራንስፖርት ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠርም የጎላ ሚና ይጫወታል።
እንዲሁም በግብርና፣ በባህላዊ ቅርሶችና እደ-ጥበብ ውጤት ባለሙያዎች፣ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የሚሰማሩ ዜጎች በቱሪዝም ፍሰቱ በቀጥታ ይጠቀማሉ። ይህም የወጣቶችንና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በስፋት ያረጋግጣል።
የመንገድ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታን የመሳሰሉ የመሠረተ ልማት አውታሮች ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ለዘርፉ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እየተገነቡ ሲሆን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ በማሻሻልና ሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በማፋጠን ረገድም የትልቅ አስተዋጽዖ ባለቤት ሆነዋል።
በአዲስ አበባ እና በክልሎች የተገነቡት የ“ገበታ” ፕሮጀክቶችም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ቀይረውታል።
አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎች እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ እንጦጦና አንድነት ፓርክ ያሉ ፕሮጀክቶች የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም አዳዲስ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው።
እንዲሁም በከተሞች ደረጃ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለኮንፈረንስ እና ለከተማ ቱሪዝም ምቹ ዕድል በመፍጠር ለሀገራችን ተጨማሪ ገቢ እያስገኘ ይገኛል።
ለቱሪዝም ዘርፍ የሚደረግ ማንኛውም ኢንቨስትመንት የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጽኑ መሠረት ላይ የመትከል አቅም ያለው የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለዘርፉ ስኬታማነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይገባዋል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: