Search

ኢትዮጵያ መሽኮርመምን የተሻገረ አዲስ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ እየተከተለች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

እሑድ ነሐሴ 03, 2018 128

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በተለይም በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል ከነበረው መሽኮርመም እና ማቅማማት በመውጣት ብሔራዊ ጥቅሟን እና ፍላጎቷን በግልጽ የሚያስከብር አዲስ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ እየተከተለች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ መንግሥት በቀይ ባሕር ላይ ያለውን መብት፣ የተሳትፎ ድርሻ እና የውኃ ላይ መውጫ ፍላጎት በግልጽ ማሳወቁን ገልጸው፣ ይህ ፍርሃትን ወደ ጎን የተወ አዲስ የዲፕሎማሲ አካሄድ ተጨባጭ ፍሬ እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያ ጥያቄ እውነተኛ እና ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን እየተረዳ መምጣቱን ጠቁመው፣ ይህ ሁኔታ እንደ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ሊወሰድ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው፣ የመደመርን ፍልስፍና ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ አንስተዋል። የመደመር እሳቤ ሀገራችንን ከለቅሶ እያወጣት እና ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ሪፎርሞች እንደ ጠንካራ መሠረት እያገለገለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህ ፍልስፍና የውጭ ግንኙነትን በአዲስ መልክ ለመምራት አቅም መፍጠሩን ገልጸው፣ ሐሳቡ ወደ ዓረብኛ፣ ሩሲያኛ፣ ቻይንኛ እና ኡርዱ (የፓኪስታን ቋንቋ) ጨምሮ ከአሥር በላይ በሆኑ የዓለም ቋንቋዎች ተተርጉሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተቀባይነት ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡

ሌሎች ሀገራት ጭምር "ይህ ሐሳብ ለኛም ያስፈልገናል" እስከማለት መድረሳቸውን ጠቅሰው፣የመደመር ሐሳብን የሚነቅፉ አካላት እንኳን ይዘቱን በጥልቀት ሲመረምሩት ከፍተኛ ዕውቀትን፣ ታሪክን፣ ባህልን እና ማንነትን አምቆ የያዘ መሆኑን እየተረዱት መምጣታቸውን አመላክተዋል።

በዚህም የመደመር ፍልስፍና በተግባር ችግሮችን እየፈታ እና ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: