ኢትዮጵያ በዕድገት እና በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሕልውና ያህል ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመቋቋም እና የሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት የመጣል ግዙፍ ሀገራዊ ራዕይ ይዞ የተነሳው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዋናነት ይጠቀሳል።
ይህ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ሽግግር የሚያፋጥን የሁለንተናዊ ብልፅግና መሠረት ነው።
ለበርካታ ዓመታት የደረሰውን የደን መመናመን እና የአፈር መሸርሸር ለመግታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሄክታር መሬቶች አረንጓዴ በመልበሳቸው የመሬት መሸርሸር እንዲቀንስ፣ የአፈር ለምነት እንዲመለስ፣ የከርሰ-ምድር ውሃ መጠን እንዲያድግ እና የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በሠራችው ሥራ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ አካል በመሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ መቻሏን በተግባር አስመስክራለች።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረቱን የደን እንጨቶችን ብቻ ሳይሆን፣ ለምግብነት እና ለኢኮኖሚ ጥቅም የሚውሉ የፍራፍሬ፣ ቡና እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ተክሎች ላይ በማድረጉ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ይገኛል።
የአቮካዶ፣ ማንጎ እና የፓፓያ ችግኞች በስፋት መተከላቸው የቤተሰብን አመጋገብ ማሻሻል ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ገበያ እና ለውጭ ኤክስፖርት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
የችግኝ ማፍላት፣ የተከላ እና የእንክብካቤ ሥራዎችም ለብዙ ሚሊዮን ወጣቶች እና ሴቶች የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ ሆነዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ትልቁ ስኬት ቁሳዊ ከሆኑ ውጤቶች ባለፈ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያመጣው የአስተሳሰብና የባህል ለውጥ ነው።
መርሐ ግብሩ የፖለቲካ፣ የብሔር እና የኃይማኖት ልዩነቶችን አሻግሮ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንድ የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ያሰባሰበ የሕዝባዊ ንቅናቄ ተምሳሌት ጭምር ነው።
ልጆች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት ወጥተው ችግኝ ሲተክሉ የሚታየው ሕብረት ሀገራዊ መግባባትን እና የወደፊት ተስፋን የሚገነባ ትልቅ አዎንታዊ ኃይል ሆኗል።
ይህ የዛሬን ችግር ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚደረግ የረጅም ጊዜ መዋዕለ-ነዋይ ነው። ተክለን የምናሳድገው እያንዳንዱ ችግኝ የተፈጥሮ ሀብታችንን ከመጠበቁም በላይ የኢኮኖሚ አቅማችንን ያጠናክራል።
ኢትዮጵያ ወደተሟላ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ ስኬታማ የሚሆነው አካባቢዋን ስትንከባከብና አረንጓዴ ልማትን የዕለት ተዕለት ባህሏ ስታደርግ በመሆኑ፣ መርሐ ግብሩ የሀገራዊ እድገታችን ወሳኝና የማይነጠል ተግባር ሆኖ ይቀጥላል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: