Search

የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት የትኛውንም የፖለቲካ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስችላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

እሑድ ነሐሴ 03, 2018 128

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት የዴሞክራሲ ምህዳሩ በሰፊው መከፈቱንና ይህም በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር የተረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለዚህም እንደ ማሳያ ያነሱት የመንግሥትን አካታችነት ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ተወዳድረው ማሸነፍ ላልቻሉ ተቃዋሚዎች ጭምር በካቢኔ ውስጥ ቦታ በመስጠት በጋራ ሀገርን የመገንባት ሥራ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ማንኛውም ዜጋ በሀገራዊ የምክክር መድረኮች እና በሚዲያዎች ላይ ቀርቦ ሐሳቡን በነጻነት መግለጽ የሚችልበት ዕድል መፈጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከለውጡ በኋላ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር መፈታታቸው የዴሞክራሲው መገለጫ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ በለውጡ የተፈቱት አንዳንዶቹ አካላት፣ ትናንት ካሰሯቸው እና ሲያሰቃዩዋቸው ከነበሩ ኃይሎች ጋር በማበር ሀገርን ለማተራመስ መሞከራቸው እጅግ አስገራሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን በኦሮሚያ ውስጥ እየተደረገ ያለው የአባገዳዎች የሰላም ጥረት የዚሁ ሰላማዊ የውይይት መፍትሔ አካል መሆኑን አውስተዋል።

አንድ የፖለቲካ ኃይል አናሳ ስለሆንኩ ተጨቆንኩ ወይም ብዙኃን ሆኜ ሥልጣን አጣሁ በሚል ሰበብ ወደ ትጥቅ ትግል መግባት በአሁኑ ዘመን የማይሠራ አካሄድ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ማንኛውም አካል የፖለቲካ ፍላጎቱን በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይት እና በሕዝብ ተሳትፎ ማሳካት እንደሚችል ጥሪ አቅርበዋል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: