ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያጋጠሟት ሁለገብ ፈተናዎች ሳይበግሯት ትኩረቷን በታላላቅ የልማት ውጥኖች እና በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ በማድረግ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ከፍታለች።
ሀገራችን በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፋ የተያያዘችው የብልፅግና ጎዳና ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመሳሰሉ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች እና በሚታዩ ተጨባጭ ስኬቶች የታጀበ ሆኗል።
እየተተገበረ ያለው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓትን ጨምሮ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተወሰዱት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መስፋፋት እና የፋይናንስ ተዳራሽነት ሀገራዊ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
በተለይም በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አማካኝነት በርካታ የሕዝብ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ መደረጉ፤ የሥራ ቅልጥፍናን ከማሳደጉም በላይ የዜጎችን እንግልት በእጅጉ ቀንሷል።
በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት፣ የኤርፖርቶች ማስፋፊያ፣ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች እንዲሁም 'የገበታ ለትውልድ' የቱሪዝም መዳረሻዎች ዘመናዊና ማራኪ ሀገራዊ ገጽታን በመፍጠር ረገድ ፈጣን ለውጥ አምጥተዋል።
በሌላ በኩልም በግብርናው ዘርፍ በበጋ ስንዴ ልማትና በምርት ስብጥር የተመዘገቡት አበረታች ስኬቶች፣ ሀገራችንን በምግብ ራስን ወደ መቻል ምዕራፍ በፍጥነት እያሸጋገሯት ይገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የበጎ ፈቃድ ሥራዎችና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸው፤ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለዘላቂ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ትልቅ መሠረት ጥሏል።
ከፈተናዎች ባሻገር የታዩት እነዚህ የልማት ስኬቶች ኢትዮጵያን ነገ ይበልጥ ተስፋማ የሚያደርጉ ናቸው። የተጀመሩት ታላላቅ የልማት እንቅስቃሴዎችና የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ተጠናክረው ሲቀጥሉ፣ ሀገራችን የያዘችውን የብልፅግና ራዕይ በተሟላ ሁኔታ እንደምታሳካ የተጣለውን ጠንካራ መሠረት ማየት በቂ ማረጋገጫ ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: