Search

የፀረ ሌብነት ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!

ሰኞ ነሐሴ 04, 2018 72

ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመደመር ዕሳቤ ወደ ተግባራዊ የለውጥ ምዕራፍ ከተሸጋገረች ወዲህ፣ እጅግ አስደናቂ፣ መጠነ ሰፊ እና በብዝኃ መልክ የሚገለጹ ታሪካዊ የልማት ድሎችን በየአቅጣጫው ማሳካት ችላለች።

ሆኖም ይህ የብልጽግና እና የሀገር ግንባታ ጉዞ ፈጽሞ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሀገራችን በርካታ ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎችን በጽናት እያለፈች ወደፊት መገስገሷን የቀጠለች ሲሆን፣ ከገጠሟት ፈተናዎች መካከል አንዱ ሌብነት፣ ሙስና እና ሕገ ወጥነት ነው።

የማኅበረሰብ ስብራት እና የዕሴቶች መሸርሸር

ይህንን የሌብነት እና የሕገ ወጥነት ፈተና ከመደመር መንግሥት ዕይታ አንጻር ስንመረምረው፣ መሠረቱ ጥልቅ የሆነ ማኅበረሰባዊ ስብራት መሆኑን እንገነዘባለን።

በማኅበረሰባችን ውስጥ ጠንካራ የነበሩ የፀረ ሌብነት ዕሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዘቀዙ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እውነተኝነትን የሚያከብረው እና ሌብነትን አጥብቆ የሚያወግዘው ማኅበረሰባዊ ሚዛን እየተዳከመ፣ ይልቁንም ሌብነትን በተዘዋዋሪ የሚያበረታታ ባሕል እያቆጠቆጠ መጥቷል።

ዛሬ ላይ ሹመኛ ካልሰረቀ ወይም በጥቅም ትሥሥር ካላለፈ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ "እንደ ሞኝ" የሚቆጠርበት እና የተንሸዋረረ ዕይታ የሚስተናገድበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ማኅበረሰቡ ጉቦ ሲጠየቅና እጅ መንሻ አቅርብ ሲባል ብቻ ሳይሆንየሻይ ሰጥቼ ጉዳዬን ቶሎ ልገላገልየሚለው አመለካከት ተዳምሮ ችግሩ ሥር እንዲሰድድ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሮለታል።

የሥርዓቱ መገለጫ ያልሆነው ፈተና

ይህ ሲባል ግን፣ የአሁኑ የመደመር መንግሥት ሥርዓታዊ የሌብነት ችግር ወይም መጠነ ሰፊ ሙስና ማጥ ውስጥ ወድቋል ማለት ፈጽሞ አይደለም። ይህ ጉዳይ እጅግ ግልጽ ሊሆን ይገባል።

ሥርዓታዊ የሌብነት ችግር የሰፈነባት ሀገር ብትሆን ኖሮ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት የታዩት ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሬት መንካት ባልቻሉ ነበር።

የመንግሥትን ሀብት፣ ፋይናንስ እና ለልማት የሚውል መሬት በከፍተኛ ቁጠባ እና ጥንቃቄ ሳያስተዳድሩ፣ እንዲሁም የግል ባለሀብቱን አቅም ከሀገር ሀብት ጋር በተቀናጀ መንገድ ሳያስተባብሩ እነዚህን ተዓምራዊ የሚመስሉ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ማከናወን ዘበት ነው።

በሥርዓታዊ ሙስና (‘ሲስተሚክ ኮራፕሽን’) ውስጥ የወደቀ መንግሥት እንዲህ ያለውን ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሞራልም ሆነ አቅም አይኖረውም። ስለሆነም፣ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ሌብነት የሥርዓቱ መገለጫ ሳይሆን፣ ሥርዓቱ እየታገለው ያለ ፈተና ነው።

የይስሙላ ትግል እና የጥቅም ትሥሥር

ይህንን እውነት ይበልጥ ለመረዳት የትናንቱን ፖለቲካዊ ታሪክ መለስ ብሎ ማየት ያሻል። ህወሓት (ወያኔ) በዚህች ሀገር ገዥ በነበረበት 27 ዓመታት ውስጥ፣ ሌብነትን በእውነት እና በተደራጀ መንገድ የተዋጋበት ታሪክ አልነበረም።

የፀረ ሙስና ትግሉ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሣሪያ ብቻ ነበር። ሥርዓቱ ለይስሙላ እና የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለማስወገድ ሲባል በሚታይ ጥቂት ድራማ ተኮር እርምጃ እና ውስጡን ግን በጠባብ የጥቅም ትሥሥር የኢትዮጵያን ሀብት በስልታዊ መንገድ ሲመዘብር እና ሀገር ሲያደማ የኖረበት ሁኔታ ነበር የነበረው።

የመንግሥት ተግባራዊ ቁርጠኝነት

አሁን ላይ ያለው መንግሥት ግን በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሌብነትን ከማውገዝ ባለፈ፣ እርምጃ ለመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይል በተግባር ደጋግሞ አረጋግጧል። በቅርቡ የተወሰዱት ሰፋፊ ኦፕሬሽኖች ይህንኑ ያረጋግጣሉ። መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማክሸፍ በሞከሩ የፋይናንስ፣ የንግድ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉ የጥቅም ትሥሥሮችን ያለምንም ማወላወል ቆርጧል።

ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴዎችን በማዋቀር፣ ተቋማትን በማጽዳት እና ኅብረተሰቡ የትግሉ አካል እንዲሆን ያለምንም መሰልቸት ጥሪ በማድረግ፣ ሥርዓቱ ሌብነትን የሚጸየፍ መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው።

እነሆ፣ የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃዎች በጥብቅ መወሰድ ጀምረዋል። አሁንም ይህ የፀረ ሌብነት ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ ፈጽሞ አይቆምም። ከላይ እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ ያለው ፀረ ሌብነት ትግል ተፋፍሞ ይቀጥላል። ይሁንና ይህንን ማኅበረሰባዊ ስብራት ለመጠገን የመንግሥት ጥረት ብቻውን በቂ አይደለም።

ማኅበረሰቡ ዕሴቶቹን ዳግም በመገንባት፣ ሹመኛን በሥራው እንጂ በዘረፈው ሀብት አለመመዘን መልመድ አለበት። የሀገርን ሀብት የሚመዘብሩ ሌቦችን ማጋለጥ፣ ጉቦን መጸየፍ፣ እና ከሕግ አካላት ጋር አብሮ በመታገል ሌቦችን አንገት ማስደፋት የእያንዳንዱ ዜጋ ሀገራዊ ግዴታ ነው። የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ዕውን የሚሆነው ሌብነትን ከመሠረቱ ነቅለን መጣል ስንችል ብቻ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: