Search

ሳይዋጋ የሚረታው፣ ግርማው ጠላትን የሚያርደው የኢትዮጵያ ዘብ

ሰኞ ነሐሴ 04, 2018 52

በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ፍልስፍና ውስጥ እጅግ የላቀው የድል ጽንሰ ሐሳብ፣ አውድማ ላይ ወርዶ ደም በማፍሰስ ማሸነፍ ሳይሆን፤ የራስን ግዙፍ እና አስፈሪ አቅም በማሳየት ጠላትን ገና በምናቡ ማሸነፍ እና ጦርነትን ከወዲሁ ማስቀረት (Deterrence) ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በለውጡ ዘመን በተደረገለት ጥልቅ እና ሁለንተናዊ ሪፎርም፣ ይህንን የዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ፍልስፍና መሠረት በማድረግ፣ ሀገራት ጠንካራ መከላከያ የሚገነቡበትን እውነተኛ ምክንያት በሚገባ በተገነዘበ መንገድ ተዋቅሯል።

ዛሬ ላይ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በረቀቀ አደረጃጀት፣ በላቀ ሳይንሳዊ ዕሳቤ እና በቴክኖሎጂ የተመጠቀ፣ እንዲሁም ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የጸዳ ሠራዊት በኢትዮጵያ ምድር ተፈጥሯል።

የዚህ ሠራዊት ዋነኛ ዓላማ በየቦታው መዋጋት ሳይሆን፣ ጠላት የሠራዊቱን አስፈሪ ክብር እና ዝና አይቶ፣ ገና ወደ ትንኮሳ ሳይገባ ሊደርስበት የሚችለውን አውዳሚ ኪሳራ በቅድሚያ በማስላት ከእኩይ ሐሳቡ እንዲታቀብ ማድረግ ነው።

የዓለም አቀፉ የውጊያ ስትራቴጂ ሽግግር

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ፣ በተለይም አሜሪካ በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብን ከተጠቀመች በኋላ፣ የዓለም የጦርነት ታሪክ እና ፍልስፍና መሠረታዊ መዋቅራዊ ሽግግር አድርጓል።

የዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ጠበብት እንዳረጋገጡት፣ እጅግ አውዳሚ የሆኑ የጦር መሣሪያዎች በዓለም ላይ በብዛት መመረታቸው እና የኃይል ሚዛን መፈጠሩ፣ አቅጣጫን ውጊያ ከማድረግ ይልቅ ጦርነትን ወደ ማስቀረት ስትራቴጂ እንድናመራ አስገድዶናል።

ለዚህም በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው የአሜሪካ ጦር ኃይሎች እና የሌሎች ታላላቅ ኃያላን ሀገራት ተሞክሮ ነው።

እነዚህ ሀገራት ግዙፍ ወታደራዊ አቅም እና ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የሚገነቡት ዘወትር ጦርነት ለመክፈት ሳይሆን፣ አስፈሪ ቁመናቸውን ያዩ ተቀናቃኞቻቸው ቀጣናቸውን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ለማስገደድ ነው።

ኃያላኑ ሀገራት ጦርነት አይፈጥሩም፣ ነገር ግን ጠላት ገና ተቋማዊ ኃይላቸውን ሲያይ አክብሯቸው ያልፋል። ውጊያም የግድ ሆኖ ከተከሰተ፣ እጅግ ዘመናዊ በሆነው ትጥቃቸው፣ በድሮን ቴክኖሎጂ እና በረቀቀው የመረጃ አደረጃጀታቸው ምክንያት፣ በአነስተኛ የሰው ሕይወት መሥዋዕትነት ተልእኳቸውን ማሳካት የሚችሉበትን አቅም ፈጥረዋል።

የዘመናዊ ትጥቅ እና ወታደራዊ ክብር ዋነኛ መገለጫም ይኸው ጦርነትን ቀድሞ የማምከን ጥበብ ነው።

ከሕልውና ስጋት መሻገር፦ የኢትዮጵያ ጽናት

ወደ ሀገራችን ነባራዊ የጂኦፖለቲካ እና የውስጥ ጸጥታ ሁኔታ ስንመለስ፣ ባለፉት ሰባት እና ስምንት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ለማስተጓጎል ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ተሞክሮ ስናይ፣ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ያነጣጠሩት ልማትን በማስተጓጎል ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገረ መንግሥቱን ሕልውና በሚፈታተኑ፣ ብሔራዊ አንድነትን በሚንዱ እና "እንደ ሀገር የመቀጠል" ታላቅ ስጋት በሚጭሩ ውስብስብ አደጋዎች ላይ ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ ከባድ ማዕበል በጽናት ተቋቁማ፣ እጅግ ፈጣን የሆነ ልማት በማረጋገጥ እና ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ዓለምን ማስደመሟን ቀጥላለች።

ይህ የሆነው በዘፈቀደ ሳይሆን፣ በእርግጥም ሳይዋጋ በሚያስፈራውና የሀገር ግርማ ሞገስ በሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን የማይበገር አቅም ነው።

ሠራዊቱ ልክ እንደ ንስር ሰፊ ክንፎቹን ዘርግቶ፣ የኢትዮጵያን ልጆች እና የሀገርን ዳር ድንበር ከአደጋ በመታደግ፣ የኢትዮጵያን የሰላምና የልማት ጉዞ አስተማማኝ አድርጎታል።

ዳግም ያንሰራራው የልዕልና ክንድ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዛሬ የደረሰበት የኤሮስፔስ፣ የባሕር ኃይል፣ የሳይበር እና የምድር ላይ ቴክኖሎጂያዊ ልዕልና፣ የፈጠረው የሪፎርም አቅም፣ እና ያካበተው ዓለም አቀፋዊ የጦር ሳይንስ ዕውቀት ውጊያን ሳይጀመር የሚያስቀር፣ ከተነሳም ጠላትን በትንሽ ኪሳራ በቅጽበት የሚያንበረክክ ሆኗል።

በአጠቃላይ፣ ባለፉት ዓመታት ሠራዊታችንን እንደገና ለመገንባት የተደረገው ሪፎርም እና የተተገበረው ፍልስፍና፣ በእርግጥም እጅግ አርቆ ያሰበ ነው።

የመከላከያ ተቋማችን ውጊያን በጉልበት ብቻ ሳይሆን በብልሃት፣ በቴክኖሎጂ እና በግርማ ሞገስ ማሸነፍ የሚችል ቀጣናዊ ልዕለ ኃይል ሆኗል።

ይህ ታላቅ የተቋም ክንድ፣ ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ታሪካዊ ልዕልናዋ እና ክብሯ የሚያመጣ፣ ሳይዋጋ የሚረታው የዘመናችን ሕያው ሀገራዊ ግርማ ሞገሳችን ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: