በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀው የ"5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ" የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ የተሳተፉ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች እና የፕሮግራሙ ምሩቃን፣ ወጣቶች ያሉትን የዲጂታል አማራጮች በመጠቀም ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ እና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ ተሞክሯቸውን ካካፈሉት ባለሙያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
ቤተልሔም ደሴ (የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ)፦ የቴክኖሎጂ ጉዞዋን ከ17 ዓመታት በፊት ገና የ10 ዓመት አዳጊ እያለች፣ ዲጂታል አማራጮች ፈጽሞ ባልነበሩበት አስቸጋሪ ወቅት መጀመሯን አስታውሳለች።
አሁን ላይ ቴክኖሎጂ በስፋት ተደራሽ በመሆኑ የዘመኑ ወጣቶች ሕልማቸውን ለማሳካት ምቹ ዕድል እንዳላቸው ገልጻለች።
ይህ ዕድል ስኬታማ የሚሆነው ግን ፈጣን እርምጃ ሲታከልበት በመሆኑ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመጠባበቅ ወጥተው ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እኩል በመራመድ አሁኑኑ የለውጥ መሪ እንዲሆኑ ጥሪዋን አስተላልፋለች።
አዝመራው ታደሰ (የኢኒሼቲቩ ምሩቅ እና ፉል ስታክ ድረ-ገጽ አልሚ)፦ ፕሮግራሙን በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ማብቂያ ላይ እንደተቀላቀለ የገለጸው አዝመራው፣ ኮድ ማድረግን መማር ከጀመረበት ጥረት ተነሥቶ በአዲስ አበባ የሚገኙ ኮደሮችን የሚያገናኝ ድረ-ገጽ እስከማበልጸግ መድረሱን ተናግሯል።
ኢኒሼቲቩ ጠንካራ መሠረት እንደጣለለት የገለጸው ምሩቁ፣ "በሰርተፍኬት ብቻ አትወሰኑ፣ የተማራችሁትን በተግባር አውሉት፣ መለማመድንም ምንግዜም ቀጥሉ፤ እውነተኛ ዕድገት የሚመጣው በዚያ ነው" ሲል ለወጣቶች አጽንኦት ሰጥቷል።
ማኅሌት ሥዩም (የኢኒሼቲቩ ምሩቅ እና የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ)፦ ፕሮግራሚንግን ለመማር እና ለማወቅ የግድ የኮምፒውተር ሳይንስ ወይም ልዩ የትምህርት ዘርፍ ምሩቅ መሆን እንደማያስፈልግ አብራርታለች።
ወጣቶች በእጃቸው ያሉትን የኢንተርኔት እና የቴክኖሎጂ መረጃዎች በመጠቀም የአካባቢያቸውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመተንተን ተግባራዊ መፍትሔ ማምጣት እንደሚችሉ አስገንዝባለች።
ለዚህም ወጣቶች ዘወትር እውቀታቸውን እንዲያድሱ፣ አጫጭር ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እና ራሳቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲያበቁ መክራለች።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: