የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ ኃይል ማስገቢያ ክፍያን በዱቤ ለሚከፍሉ ደንበኞች ሲያስከፍል የነበረውን የወለድ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው አስታወቁ።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ቀደም ሲል የዱቤ ክፍያ ጊዜው እስከ 24 ወራት የሚደርስ ሆኖ፣ ከ6 ወራት በላይ ለሚቆይ ክፍያ ከ3 እስከ 9 በመቶ የሚደርስ ወለድ ይታሰብ ነበር።
አሁን ላይ ይህ የወለድ ክፍያ ሙሉ በሙሉ መነሳቱ፤ የኃይል ማስገቢያ ክፍያን በአንድ ጊዜ መክፈል ለማይችሉ ዜጎች ትልቅ የምስራች ከመሆኑም በላይ የተቋሙን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ያደርገዋል።
በቅርቡ ሥራ ላይ በዋለው የአዲስ ቆጣሪ የዱቤ አሰራር ከሰኔ ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 19 ሺህ 231 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በአጠቃላይ ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት 664 ሺህ 505 አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ 1.1 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን ለማገናኘት ዕቅድ ይዟል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ70 ዓመታት ታሪኩ ማገናኘት የቻለው አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 5.88 ሚሊዮን መሆኑን ያስታወሱት ኢንጅነር ጌቱ፤ አሁን ላይ ግን ተቋሙ በየዓመቱ እስከ 1 ሚሊዮን ደንበኞችን የማገናኘት አቅም ላይ መድረሱን አብራርተዋል።
ይህም ተቋሙ የዜጎችን የክፍያ ጫና በማቃለል ኤሌክትሪክን ለበለጠ የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ እና የደንበኛ ተኮር አገልግሎቱን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ አገልግሎቱ የላከለን መግለጫ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: