Search

የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ተሳታፊዎችን ወደ 7 ሚሊዮን ለማድረስ የወጣቶች የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሄደ

ሰኞ ነሐሴ 04, 2018 66

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የቀረበውን የኢትዮጵያ ወጣቶች 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭን እንዲቀላቀሉ እና የክረምቱ ወቅት ከመጠናቀቁ በፊት የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ 7 ሚሊዮን ለማድረስ የተደረገውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተናጋጅነት በኢኒሼቲቩ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ይህ ዝግጅት የዘርፉን መሪዎችና ፖሊሲ አውጭዎች፣ የምስክር ወረቀት ያላቸውን የኢኒሼቲቩን ተመራቂዎች እና ወጣት ባለሙያዎችን በአንድነት ያገናኘ ነው።

ተሳታፊዎች ተሞክሯቸውን እና እይታቸውን በመድረኩ እንዲያካፍሉ መደላድልን በመፍጠርም፣ መርሐ ግብሩ በተግባራዊ ዲጂታል ክህሎት ልማት አማካኝነት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አጀንዳ ዕድገት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

መርሐ ግብሩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ላይ ባተኮረ የኤግዚቢሽን ጉብኝት የተጀመረ ሲሆን፣ በመቀጠልም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

ኃላፊዋ በንግግራቸው የወጣቶች የቴክኒክና የዲጂታል ክህሎት ብቃት ወሳኝ ሀገራዊ ሀብት መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ክረምት የኮደሮችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ ተግባራዊነት አረጋግጠዋል።

በመቀጠል በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ልምዳቸውንና እይታቸውን ያካፈሉ አራት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ፓናሊስቶቹም፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ / አብዮት ባዩ፣ የጊሮ (gheero) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቤተልሔም ደሴ፣ እንዲሁም የኢኒሼቲቩ ምሩቃን የሆኑት አዝመራው ታደሰ እና የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ማኅሌት ሥዩም ነበሩ።

ተሳታፊዎችና ወጣቶች ክህሎታቸውን ያለማቋረጥ እንዲያሳድጉ፣ በተግባር ላይ ያተኮሩ መፍትሔዎችን እንዲያበለጽጉ እና በኢትዮጵያ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ዕድገትና ፈጠራ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች አበረታተዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: