ሀገራዊ ምክክር ያስፈለገው የአንድ ሀገር ዜጎች መሠረታዊ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ስላላቸው አይደለም። ይልቁንም አብረው እንዲመክሩ የሚያደርጋቸው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያየ ሐሳብ (አመለካከት) በማራመዳቸው ነው።
ስለዚህ ሒደቱ የተለያየ ልምድ፣ ዕይታ እና ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ስለ ጋራና የወደፊት ሀገራቸው የሚያስቡበትን ዕድል ይፈጥራል።
በሀገራዊ ምክክር ሒደት ውስጥ ሁሉም ተመካካሪ የራሱ ታሪክ አለው። በሒደቱ አንዱ ሌላውን ለማድመጥ ብሎም ለማወቅ ካልሞከረ ከሐሳቡ ጀርባ ያሉ ፍላጎቶችን ሊያውቅ አይችልም፤ ያም እርስ በርስ ለመተዋወቅ እና ለመግባባት የሚደረገውን ጥረት ምሉዕ እንዳይሆን ያደርገዋል።
የልዩነት ጥንካሬ የሚገኘውም እዚህ ላይ ነው። በሀገራዊ ምክክር ሒደት ውስጥ የሐሳብ ብዝኃነት መኖሩ እያንዳንዱን ሐሳብ እንድንፈትሽ መንገድ ይጠርጋል። ሌሎችን ለማዳመጥ፣ ጥያቄ ለመጠየቅ እና የማናውቀውን ለመረዳት ዕድል ይሰጠናል። ይህም የጋራ ግንዛቤን በማሳደግ የተሻሉ የጋራ ውሳኔዎችን ለመወሰን በር ይከፍታል።
ነገር ግን የሐሳብ ልዩነት መኖር ብቻውን ለሀገራዊ ምክክር መጎልበት በቂ አይሆንም። የሐሳብ ልዩነቶች ትርጉም ያለው ጥቅም ሊያመጡ የሚችሉት ተመካካሪዎች የሐሳብ ልዩነቶቻቸውን በመከባበር ማስተናገድ ሲችሉ እና እርስ በርስ ሲደማመጡ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል።
ልብ እንበል! የሀገራዊ ምክክር ዓላማ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ሐሳብ እንዲያራምድ ማድረግ አይደለም። ሒደቱ ልዩነቶችን ወደ መማማር፣ መግባባት እና ችግር መፍቻ አቅም በመቀየር የጋራ የሆነ የመግባባትን መንገድ የምንቀይስበት መሆኑን ማስተዋል ይገባል።
ስለዚህ ሀገራዊ ምክክር “ልዩነቶቻችንን በበቂ ሁኔታ ተረድተን እንዴት የጋራ መንገድ እንፍጠር?” ብሎ ይጠይቃል።
የተለያዩ ዕይታዎች በአክብሮት ሲደመጡና በጥሞና ሲታዩ፣ ሀገራዊ ምክክር ወደ ተሻለ የመግባባት መንገድ፣ ሰፋ ያሉ መፍትሔዎች ወደ ማምጣት እና ወደ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ሊያመራ ይችላል።
እናስታውስ! የሐሳብ ልዩነት የሀገራዊ ምክክር መለያ ቀለም ነው። ነገር ግን በምክክር ሒደት ውስጥ ልዩነቶችን የምናስተናግድበት መንገድ የሠለጠነ እና ሰብአዊነት የተሞላው ሊሆን እንደሚገባ መዘንጋት የለብንም!
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: