ኢትዮጵያ አሁን ላይ የደረሰችበት የሕዝብ ቁጥር፣ እጅግ ሰፊ የሆነው የወጣት ኃይል እና ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፤ ሀገራችን አህጉራዊ የአምራችነት ማዕከል ለመሆን ያላትን ምቹ ሁኔታ በግልጽ ያሳያሉ።
ይህ እምቅ አቅም ሀገር በቀል የኢንዱስትሪ ልማት ራዕይ ሲደገፍ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድ ማዕከል የማድረግ ከፍተኛ ዕድል አለው።
ይሁን እንጂ ይህንን አቅም ወደ ሙሉ ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ለመቀየር እና በአፍሪካ ቀንድ ያለንን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና ከፍ ለማድረግ የራስ የባሕር በር ባለቤት መሆን የህልውና ያህል ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
ቀጥተኛ እና አስተማማኝ የባሕር በር መገኘት በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚያችን ምሰሶ የሆኑትን እንደ ቡና ያሉ የግብርና ምርቶችን፣ ጨርቃጨርቅን እና ማዕድናትን በከፍተኛ ፍጥነት እና ቅልጥፍና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላል።
በአሁኑ ወቅት የሎጅስቲክስ መዘግየት እና ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ወጪዎች በምርቶቻችን የዋጋ ተወዳዳሪነት ላይ ትልቅ ጋሬጣ ሆነው ይገኛሉ።
የራስ የወደብ አማራጭ ሲረጋገጥ ግን እነዚህ አላስፈላጊ ወጪዎች በመቀነሳቸው ምርቶቻችን በአህጉራዊው ገበያ ላይ እጅግ በቅናሽ ዋጋና በጥራት መቅረብ ይችላሉ።
ይህ ስትራቴጂያዊ ዕድል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ላይ የሚፈጥረውን ሰፊ የገበያ ትስስር እንድትመራ ያደርጋታል።
ከአህጉራዊ ተወዳዳሪዎቻችን ቀድመን የአፍሪካን የፍጆታ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ እና ጠንካራ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የባሕር በር መኖሩ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከፖለቲካዊ ፍላጎት ባለፈ የዜጎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያሳልጥ እና የኢትዮጵያን አህጉራዊ አምራችነት ወደ እውነት የሚቀይር ብሔራዊ የልማት ራዕይ ነው።
ይህ እርምጃ ሀገር በቀል የአምራችነት አቅምን በሙሉ ፍጥነት በመጠቀም ምርቶቻችንን ያለ ሎጅስቲክስ ማነቆ ለአፍሪካ እና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: