Search

"ነፃነት ሕግ ነው"፡ ጥንታዊው የቦረና ፍልስፍና ለኢትዮጵያ ሰላም

ሰኞ ነሐሴ 04, 2018 72

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋር ባደረጉት ሰፊ ቆይታ፣ የሀገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሽግግር እና የመንግሥት ግንባታ ሂደት ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር በማዛመድ ጥልቅ ፍልስፍናዊ ዕይታን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ቦረና ስለ ነፃነት እና ሕግ ያለው ፍልስፍና ነው። በንግግራቸውም፣ "ቦረና 'ነፃነት ሕግ ነው፤ ሕግ ደግሞ ሰላም ነው' እንደሚለው ሁሉ፣ የፖለቲካ ነፃነት ወደ ምክክር ያድጋል፤ ምክክር ደግሞ ወደ ሕግ የበላይነት ያድጋል" ሲሉ ሂደቱን ገልጸውታል።

ይህ አነጋገር ነፃነትን፣ ምክክርን፣ የሕግ የበላይነትን እና ሰላምን በቅደም ተከተል የተሳሰሩ የፖለቲካ ዕድገት ምዕራፎች አድርጎ የሚያቀርብ ነው። ትስስሩም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና የዴሞክራሲ ግንባታ መሠረታዊ ፍኖተ ካርታን የሚያመለክት ነው።

በቦረና ማኅበረሰብ ጥንታዊ የገዳ ሥርዓት እና አስተዳደር ውስጥ "ነፃነት ሕግ ነው" የሚለው መርሕ መሠረታዊ የማኅበረሰብ ምሰሶ ነው። በቦረና ባህል ነፃነት ማለት ሕግ እና ሥርዓትን ጥሶ በፈለጉት መንገድ የመመላለስ ወይም የሥርዓተ-ዐልቦነት መገለጫ አይደለም። ይልቁንም በማኅበረሰባዊ ስምምነት እና በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚኖር የተከበረ ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብት ነው።

በየስምንት ዓመቱ በሚካሄደው ከፍተኛ ሕዝባዊ ጉባኤ ወይም "ጉሚ ጋዮ" ላይ የማኅበረሰቡ አባላት ሙሉ የሐሳብ ነፃነት አግኝተው በግልጽ ይወያያሉ፤ አዳዲስ ሕጎችን (ሴራ) ይደነግጋሉ፤ ነባሮቹን ደግሞ ያሻሽላሉ።

በዚህ የጋራ ሂደት ውስጥ ነፃነት በስፋት ይንጸባረቃል፤ ነገር ግን ነፃነት በምክክር በኩል በማለፍ ጥብቅ የሕግ የበላይነትን ይፈጥራል። የተገነባው የሕግ የበላይነት ደግሞ የመጨረሻ ግቡ የሆነውን እና "ናጋ ቦረና" (የቦረና ሰላም) የሚባለውን ዘላቂ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ደኅንነታዊ ሰላም ያረጋግጣል።

ይህንን የቦረና ጥንታዊ የሕግ እና ሰላም ፍልስፍና ወደ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ስናመጣው፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ምኅዳር ሂደት በግልጽ እንድንገነዘብ ያደርገናል። በኢትዮጵያ በተካሄደው ሀገራዊ የፖለቲካ ማሻሻያ ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር ተከፍቷል።

ይሁን እንጂ በሀገራችን እንደዚህ ዓይነት ነጻነቶችን ለማስተዳደር የተገነቡ ተቋማት ባለመኖራቸው ይህ የተገኘው ነፃነት ገና ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ግጭቶችን እና የደኅንነት ፈተናዎችን አስከትሏል።

ይህም ነፃነት ብቻውን በቂ አለመሆኑን፣ እንዲሁም ያለ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ እና የጋራ የምክክር ባህል የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ እንደማይችል በግልጽ አሳይቷል።

ይህንን በነፃነት ስም መጣውን ምስቅልቅል በዘላቂነት ለመፍታት እና የቦረናን አቃፊ አስተሳሰብ ለሀገር ግንባታ ለመጠቀም፣ ሀገራችን ነፃነትን ወደ አሳታፊ ምክክር የማሸጋገር ሰፊ ታሪካዊ ሥራ ውስጥ ገብታለች።

ለዚህ ትልቁ ተጨባጭ ማሳያ ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው። ኮሚሽኑ ልክ እንደ ቦረናው 'ጉሚ ጋዮ' ሁሉ፣ ልዩነቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ ሀሳቦችን ይዞ ወደ አንድ ጠረጴዛ በመምጣት፣ በሀገራዊ መሠረታዊ ጉዳዮች፣ በሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎች እና በዜጎች አብሮ መኖር ላይ አካታች ውይይት እንዲደረግ ታሪካዊ መደላድል ፈጥሮ ዋናውን የምክክር ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በርካታ የጦር መሣሪያ ያነሱ አካላት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኅብረተሰቡ እየተቀላቀሉ መሆናቸው ሀገራችን ከኃይል ወደ ምክክር እና ውይይት እየተሸጋገረች መሆኗን የሚያሳይ ሌላው ተጨባጭ ማስረጃ ነው።

ይህ በነፃነት ተጀምሮ በሀገራዊ ምክክር እየጎለበተ ያለው ሂደት በስኬት ሲጠናቀቅ የሚኖረው በጎ ውጤት እጅግ የላቀ ነው። የመጀመሪያው ትልቅ ውጤት፣ በፖለቲካ ኃይሎች እና በሕዝብ መካከል የጋራ መተማመን መፈጠሩ እና የጠብመንጃ ፖለቲካ ታሪክ ሆኖ መቅረቱ ነው።

ሁለተኛው እና ዋናው ውጤት ደግሞ፣ በምክክር የጸደቀ እና በሕዝብ ተቀባይነት ያለው ጠንካራ የሕግ የበላይነት መስፈን መቻሉ ነው። የሕግ የበላይነት ሲሰፍን የዜጎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተጠበቁ ይሆናሉ፤ የፍትሕ ተቋማት ገለልተኛነታቸው የተረጋገጠ ይሆናል፤ መቼም የማይናወጥ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ያረጋግጣል።

ይህም ዘላቂ ሰላም እና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ብልፅግናዋን ለማፋጠን፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የዜጎቿን ሕይወት በጥራት ለመቀየር ሙሉ አቅሟን እንድትጠቀም ያስችላታል።

ስለሆነም ነፃነትን በምክክር በማጎልበት እና ምክክርን ወደ ሕግ የበላይነት በማሳደግ የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ አንድነት ማረጋገጥ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅ የዘመኑ የዜግነት እና ሀገራዊ ኃላፊነት ነው።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: