ሀገራዊ ምክክር በአንድ ጀምበር ተጀምሮ የሚያልቅ አጭር ሂደት አይደለም። በዚህም የተነሣ ሁሉም የተለዩ ጉዳዮች (ስምንቱም አጀንዳዎች) በአሁኑ ምዕራፍ የግድ ተጠናቅቀው እልባት ላያገኙ ይችላሉ፤ አፈታታቸውም የተለያየ ሊሆን ይችላል።
አንዳንድ ጉዳዮች ረዘም ያለ ጊዜ የሚፈጁ፣ የቀጣዩን ትውልድ ተሳትፎ (ተዋጽኦ) በብርቱ የሚጠይቁ፣ እንዲሁም ወደ ሚቀጥለው ትውልድ ሊሻገሩ የሚችሉ ናቸው።
የምክክር ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ ተጀምሮ በጥሩ መሰረት ላይ እየተጓዘ ይገኛል።
እስካሁን ያለው ውይይት አንድ ወር ገደማ የፈጀ ሲሆን፣ አሁን ያለውን ምዕራፍ በቀጣዮቹ አንድ ወይም ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማገባደድ ታቅዷል።
ውይይቱ የሚጠናቀቀው የ4 ሺህ ተመካካሪዎችን ሐሳቦች አጠናቅሮ እና አደራጅቶ ወደ ተግባሪው አካል በመላክ ነው።
ኮሚሽኑ ሐሳቦቹን ለተግባሪው አካል ከመላክ ባለፈ፣ ውሳኔዎቹ እና ሐሳቦቹ በየደረጃው መተግበር አለመተግበራቸውን በቅርበት ይከታተላል።
ለሂደቱ ስኬት ትልቅ አቅም ላበረከተው ሕዝብ፣ የክትትሉን ውጤት እና የትግበራውን ደረጃ በተመለከተ ግብረ-መልስ የማሳወቅ እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሂደት ሥራ ይሠራል።
በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሦስት ቀናት ውስጥ በሚኖረው መገናኘት፣ ውይይቱ እርምጃዎችን ወደፊት ተራምዶ አስደሳች እና ተስፋ ሰጪ ምክረ ሐሳቦች ላይ በመድረስ ለሕዝቡ ለማብሰር ኮሚሽኑ ተስፋ ያደርጋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: