ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የምታካሂደው የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ትራንስፎርሜሽን የሩቅ ምኞት ሳይሆን አሁን ላይ መሠረቱ ተጥሎ ወደ ተግባር የተሸጋገረ ተጨባጭ እውነታ ነው።
ለዘመናት የቆዩ መዋቅራዊ መሰናክሎችን በመስበር ትልልቅ ፕሮጀክቶችን አቅዶ የመጀመር እና በስኬት የመጨረስ አዲስ ባህል አዳብራለች ኢትዮጵያ።
ይህ ሂደት ሀገራችን ከውጭ ጥገኝነት በማላቀቅ፣ በአፈር ማዳበሪያ፣ በተፈጥሮ ጋዝ፣ በኒውክሌር ኢነርጂ እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ አዲስ ተስፋና አህጉራዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትን እያበሰረ ይገኛል።
የዚህ ታላቅ ሽግግር ዋና ማዕከል ደግሞ ሀገራችንን ከጥገኝነት ማላቀቅ እና የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱ መሰረት ከግብርና መሆኑን ለይቶ ማየት እንደማይቻል የተረዳው የልማት አቅጣጫ፣ የግብርና ምርታማነትን አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ኩንታል በእጥፍ በመጨመር 1 ቢሊዮን ኩንታል ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል፡፡
ለዚህ ደግሞ የክላስተር እና የመስኖ እርሻን ከተሻሻሉ ዘሮች ጋር ማቀናጀት ብቻ ሳይሆን ዋናውን ግብዓት የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በሀገር ውስጥ ለማምረት የፋብሪካ ግንባታ ተጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት የፋብሪካ ግንባታ ጀምረናል፣ ይህም ሙሉ ምላሽ ያመጣል ብዬ አስባለሁ፤ ማዳበሪያ ማምረት መቻል አዲስ ታሪክ ነው" በማለት የዘርፉን ወሳኝነት ያስረዳሉ።
ይህ ስኬት ሀገራችንን ከውጭ ምንዛሬ ጫና ከመታደጉም በላይ በበጋና በክረምት የመስኖ ልማት በምግብ ራሷን የቻለች ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ይገነባል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለ60 ዓመታት ያህል ስታካሂድ የቆየችውን የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ አጠናቅቃ ወደ ምርት መሸጋገሯ ሌላው ሥርነቀል እርምጃ ነው። አሁን ላይ የተፈጥሮ ጋዝ ምርቱ ለፋብሪካዎች ግብዓት እና ለኃይል ማመንጫነት እየዋለ ይገኛል።
በቅርብ ወራት ውስጥ ደግሞ ተሸከሪካሪዎች ከናፍጣ ወደ ጋዝ አጠቃቀም በመሸጋገር በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የወጪ ቅናሽ ያመጣሉ። ከዚህ በተጨማሪም በቢሾፍቱ እየተገነባ ያለው ግዙፍ ዓለምአቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ የአለምን ትኩረት የሳበ ሲሆን ኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት የመፈጸም ከፍተኛ አቅም እንዳላት በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የነገዋን የኢንዱስትሪና የኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ታሪካዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ኃይል ማመንጨት የሚያስችላትን መሠረተ-ልማትና ኢንዱስትሪ ለመገንባት በዝግጅት እና በውይይት ደረጃ ላይ መገኘቷ ለአህጉራችን አዲስ ምዕራፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በኒውክሌር ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ከኒውክሌር ፓወር ሃይል ማመንጨት እንደምትችል አቅዳ፣ ኢንዱስትሪዋን መገንባት እየተነጋገረች ነው፤ ይሄ በራሱ በጣም የተለየ ሃሳብ ነው፣ ይህ አዲስ ታሪክ ነው፣ በአፍሪካ ደረጃም ትልቅ ታሪክ፣ በኢትዮጵያም ደረጃ ትልቅ ታሪክ ነው" ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከጥቂት የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ባለቤቶች ተራ ከመሰለፏም በላይ ለፋብሪካዎችና ለኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ኃይል ታቀርባለች።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የምታስመዘግበው ዕድገት የበርካታ ዘርፎች ቅንጅት ውጤት ይሆናል። ግብርናው በሀገር ውስጥ ማዳበሪያ ሲደገፍ፣ ትራንስፖርቱና ኢንዱስትሪው በሀገር ውስጥ ጋዝ ሲንቀሳቀስ፣ የኃይል ዘርፉ ደግሞ በኒውክሌርና በታዳሽ ኃይል ሲጎለብት ሀገራችን ከአነስተኛ አስተሳሰብ ወጥታ ወደ ታላቅ የኢኮኖሚ ጉልበት ትሸጋገራለች።
እነዚህ በተግባር የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በስኬት ተጠናቀው ለወደፊቱ ብሩህ መሠረት የሚጥሉ በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያን አለምአቀፋዊ ገጽታ እና የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀይሩ ይሆናሉ።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: