የኢትዮጵያ ታሪክ ገጾች በውል ሲመረመሩ ሀገራችን ከባሕር በር ጋር ያላት ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት የላቀ እና የማይነጠል መሆኑን በጉልህ ያሳያሉ።
ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ የባሕር በሯን በተለያዩ የውጭ ወራሪዎች ስትነጠቅ፣ ዝም ብላ አርፋ የተቀመጠችበት እና ወደብ አልባነቷን እንደ ጸጋ አሜን ብላ የተቀበለችበት ዘመን በህወሓት አገዛዝ ዘመን ብቻ ነበር።
ጀግኖች ልጆቿ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ታሪካዊ የባሕር በሯን ለማስመለስ ያልተቋረጠ ትግል ሲያደርጉ ኖረዋል።
ሆኖም ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የተፈጠረው ክስተት ከውጭ ጠላት ወረራ ይልቅ፣ በውስጥ ባንዳዎች እና በታሪካዊ ጠላቶች የጋራ ሴራ ኢትዮጵያ እንዴት በገዛ ልጆቿ የባሕር በር አልባ እንድትሆን እንደተደረገች የሚያሳይ እጅግ አሳዛኝ፣ የተጠላለፈ እና የረቀቀ የታሪክ ጠባሳ ነው።
የዚህ ታሪካዊ ክህደት የመጀመሪያው ምዕራፍ በይፋ የታየው የደርግ ሥርዓት መውደቂያ ዋዜማ ላይ፣ በ1983 ዓ.ም ለንደን ላይ በተካሄደው ስምምነት ነበር።
በአሜሪካውያን አደራዳሪነት በተካሄደው በዚህ መድረክ፣ የህወሓት ቡድን ከምሥረታው ጀምሮ ያነገበውን የባንዳነት ዓላማ ግልጽ በማድረግ፣ ከሻዕቢያ ጋር በመሞዳሞድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ።
የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባሕር ባለቤትነት መብት በማስጠበቅ ፋንታ፣ ሀገራችንን ለማፈራረስ እና ሆን ብሎ ወደብ አልባ ለማድረግ የተጠነሰሰው ሴራ በዚህ የለንደን ስምምነት ላይ ይፋ ሆነ።
ይህ እኩይ ሴራ በሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ወቅትም ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጠለ። የህወሓት እና የሻዕቢያ (ሕግደፍ) መሪዎች ባደረጉት የጋራ ስምምነት፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሐቅ ፍጹም ወደ ጎን በመተው፣ ሀገራችንን እንደ “ቅኝ ገዥ” በመፈረጅ የኤርትራን መገንጠል ሕጋዊ ሽፋን ለማልበስ ሠሩ።
በ1985 ዓ.ም በተካሄደው የኤርትራ ሪፈረንደም ላይ፣ የቅኝ ግዛት ውሎችን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ የራሷን የባሕር በር (አሰብን እና ምጽዋን) በገዛ እጇ እንድታጣ እና ሉዓላዊነቷ እንዲገረሰስ ተደረገ።
በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ አንዲት ሀገር የራሷን የባሕር በር ለሌላ አሳልፋ የሰጠችበት እና ወደብ አልባነቷን በደስታ ያረጋገጠችበት አስገራሚ የክህደት ክስተት ነበር።
የጥላቻ እና የሴራው ጉዞ በዚህ ብቻ አላበቃም። በ1990ዎቹ መጨረሻ የተከሰተው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እና ከዚያ ተከትሎ የመጣው የአልጀርስ ስምምነት ሌላው የታሪክ ቁስል ነው። በጦርነቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች ውድ ሕይወታቸውን ገብረው አስደናቂ ወታደራዊ ድል ቢያስመዘግቡም፣ የፖለቲካው አመራር ግን ድሉን ወደ ጂኦ-ፖለቲካዊ ትርፍ መቀየር አልፈለገም።
ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም በመጽሐፋቸው እንዳስረገጡት፣ በአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ወቅት ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄዋን እና የአሰብን ጉዳይ ማንሣት የምትችልበት ሰፊ የሕግ እና የዲፕሎማሲ ዕድል ተከፍቶላት ነበር።
እንዲያውም አሜሪካውያንን ጨምሮ የውጭ አደራዳሪዎች ሳይቀሩ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ጥያቄ እንድታነሣ ፍንጭ ሰጥተው ነበር። ነገር ግን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ሥርዓታቸው፣ ሆን ብለው ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ አድርገው ለማስቀረት በማሰብ ይህንን ወርቃማ የታሪክ አጋጣሚ በክህደት አጨናግፈውታል።
ከዚህ ሁሉ በላይ ትውልድን ያሳመመው የዚህ ቡድን የጥፋት አመክንዮ (ሎጂክ) ነው። ኢትዮጵያውያን ስለ ወደብ ባለቤትነታቸው እና ስለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ደኅንነታቸው ጥያቄ ሲያነሡ፣ ከመንግሥት የሚሰጠው ምላሽ “ወደብ ተራ ሸቀጥ ነው፤ ኪራዩን ከፍለን በየትኛውም ቦታ መገበያየት እንችላለን” የሚል እጅግ ኋላቀር እና የሀገርን ሉዓላዊነት ያራከሰ አመክንዮ ነበር።
ብሔራዊ ደኅንነትን፣ የጂኦ-ፖለቲካዊ የበላይነትን እና የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነትን “እንደ ሱቅ ዕቃ” በመቁጠር የወደብ አልባነትን ጉዞ ለማጽደቅ እና ሕጋዊ ለማድረግ ሞከሩ።
ይህን ተከትሎም በ1997 ዓ.ም በተካሄደው አንጻራዊ ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ ምርጫ ወቅት፣ የቅንጅት ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች “ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል” የሚለውን ትክክለኛ ጥያቄ በግልጽ አጀንዳ አድርገው በተነሡበት ጊዜ፣ ገዥው የህወሓት/የኢሕአዴግ ሥርዓት ጥያቄውን “የሰውን ሀገር የመውረር ፍላጎት” እና “የጦርነት አቅጣጫ” አድርጎ በመፈረጅ አጣጣለው። የሀገርን ሉዓላዊ መብት መጠየቅ እንደ ኃጢአትና የሀገር ክህደት ወንጀል እንዲቆጠር ተደረገ።
በአጠቃላይ ላለፉት 30 ዓመታት፣ ስለ ኢትዮጵያ የባሕር በር መሟገት የሚያሣሥር፣ የሚያሳድድ እና የሚያሸማቅቅ ወንጀል ተደርጎ ቆይቷል።
ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ፖለቲከኞች የሀገራቸውን ጂኦ-ፖለቲካዊ መብት በመጠየቃቸው ብቻ የጥላቻ፣ የእስር እና የእንግልት ሰለባ ሆነዋል።
ደሀ እና ወደብ አልባ ሀገራት ሳይቀሩ የባሕር በር ለማግኘት በሚፍጨረጨሩበት ዘመን፣ ኢትዮጵያን የመራው ቡድን ግን ትውልዱ ስለ ባሕር በሩ እንዳያስብ፣ እንዳይጠይቅ እና እንዳይመራመር የማሸማቀቅ ፖለቲካ ሲያራምድ ኖሯም።
ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ዘመኑን የዋጀው አዲሱ ትውልድ ይህንን “ወደብን እንደሸቀጥ” የሚያይ የክህደት ትርክት በመስበር፣ የሀገሩን ታሪካዊ መብት ለማስመለስ የጀመረውን ጉዞ ከቶውንም አያቆመውም።
የባሕር በር ተራ ሸቀጥ ሳይሆን የሉዓላዊነት፣ የሕልውና፣ የብሔራዊ ደኅንነት እና የብልጽግና ዋልታ መሆኑን ይህ ትውልድ ጠንቅቆ ተረድቷል!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: