የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የሚያረጋግጡ መሠረቶች መሆናቸውን ገለጹ።
ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን እጣፈንታ ሲወስኑ መቆየታቸውን የገለጹት ሚኒሰትሩ፣ የኢትዮጵያዊያን ሕልውና ከእነዚህ የውሃ አካላት ጋር ከፍተኛ ቁርኝነት እንዳለው አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳታለማና እንዳትጠቀም የውጭ ኃይሎች በተለያዩ መንገዶች ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተው፣ በተመሳሳይ በሴራ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ በማድረግ ኢትዮጵያውያን ብዙ ዋጋ ሲከፍሉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
በሕዳሴ ግድብ አማካኝነት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት ከነበረው ህልማቸው መካከል አንዱን ማሳካት መቻሉን ገልጸው፣ ይህም በኢትዮጵያውያን ላይ ይደርስ የነበረውን ተጽዕኖ መስበር ያስቻለ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ላይ ሲደረጉ የቆዩ ደባዎችን ማስቀረት የቻለ የኢትዮጵያውያን ኩራት መገለጫ ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን በተለያየ ሴራ እና ተንኮል እንድታጣ ከተደረገ በኋላ ይህንን ጉዳይ ማንሳት የማይፈቀድ እና ሌላ ስም የሚያሰጥ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የባሕር በር ባለቤትነቷን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማግኘት አለብኝ ብላ ያነሳችው ጥያቄ ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የቀይ ባሕር ጉዳይ የመንግሥት ወይም የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ጉዳይ ሳይሆን ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ መሆኑን ጠቁመው፣ ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የሚያረጋግጡ መሠረቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
እንዲሁም በቀይ ባሕር አቅራቢያ የሚታዩ ዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውድድሮች እና የባሕር ላይ የደኅንነት ስጋቶችን ማቃለል የሚያስችላት መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያውያን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያሳዩትን አንድነት በቀይ ባሕር ላይም መድገም እንዳለባቸው አመልክተዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: