በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የከተማ ልማት ትውልድን የሚያሻግር፣ የሥራ ፈጠራን የሚያነቃቃ እና ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ ቱሪዝም ዝግጁ የሚያደርግ ግዙፍ ስትራቴጂካዊ እርምጃ በመሆኑ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው አዳዲስ ተስፋዎችን እየወለደ ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተተገበሩት እንደ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለትውልድ እና የኮሪደር ልማት ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አድገት በማፋጠን እና የከተሞችን ገጽታ በመለወጥ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።
በተለይም በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተጀመረውና በአሁኑ ወቅት በበርካታ ከተሞች በተሳካ ሁኔታ የተገነባው የኮሪደር ልማት ሥራ ሰፋፊ መንገዶችን መሥራት ብቻ ሳይሆን የከተማን ውበት፣ ምቾት እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በአንድ ላይ ማምጣት የቻለ የሥራ ጥራትና ፍጥነት የተስተዋለበት ስኬት ሆኗል።
ይህ ፕሮጀክት የከተሞችን የጉስቁልና ዘመን በመቀየር ልምላሜ የናፈቃቸው የአስፋልት ዳር መንገዶች የአረንጓዴ ካባ እንዲለብሱና የጨለማ ጉዞ አክትሞ በምሽት መብራቶች ደምቀው እንዲታዩ አድርጓል።
ይህ አዲሱ የከተማ ልማት ፅንሰ ሀሳብ ከተሞች እንዲያድጉ መሠረተ ልማት በቅርበት እንዲሟላ እና የእርሻ መሬቶች እንዳይጠፉ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሰፊና ማራኪ በሆኑት ኮሪደሮች ዙሪያ የተሰሩት አዳዲስ ካፌዎች፣ የንግድ ማዕከላት እና የኪነ ጥበብ ስፍራዎች የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ሌሊትና ቀን ህያው አድርገውታል።
ኮሪደሩ የቀለም ወጥነትን፣ የግንባታ ጥራትን እና የብርሃን አቅርቦትን በመጠቀም ከተሞች ንጹህ እና ውብ እንዲሆኑ እያደረገ ሲሆን፣ ሌሊት የሚያበሩ መብራቶች መኖራቸው ነዋሪዎች በነፃነትና ያለደህንነት ስጋት እንዲንቀሳቀሱ አስችሏል።
ከዚህ ጎን ለጎን ቀደም ሲል የጤና ስጋትና የቆሻሻ ማስወገጃ የነበሩ ወንዞችና የውሃ ዳርቻዎች ታሪካቸው ተቀይሮ ወደ ውበት ምንጭነት የተለወጡ ሲሆን፣ የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ ማራኪ መዝናኛ ፓርኮች፣ ሰው ሰራሽ ሀይቆች እና የህዝብ መዝናኛ አደባባዮች በመቀየር ከተማዋን ከጎርፍ አደጋ ከመታደጉም በላይ ነዋሪዎችን ከድምጽ፣ ከአየርና ከመንገድ ቆሻሻ ብክለት የፀዳ ንጹህ አየር በመስጠት የስነ ምህዳር ሚዛኑን በከፍተኛ ደረጃ ጠብቋል።
የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች በአንድ ላይ ተደምረው ከተሞቻችንን ወደ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻነት እየቀየሩ ሲሆን፣ ቱሪስቶች ወደ ታሪካዊ ቦታዎች ከመሄዳቸው በፊት በከተማው እምብርት በሚገኙ ውብ ፓርኮች እና በምሽት መብራቶች ደማቅ በሆኑ ኮሪደሮች ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ በማድረግ የከተማ ቱሪዝምን ማሳደግ ችሏል።
ከዚህ ባለፈም ይህ የልማት ስራ በግንባታ ወቅት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ መሃንዲሶች፣ ግንበኞች እና የውበት ባለሙያዎች ሰፊ የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ ከግንባታ በኋላም አዳዲስ ፓርኮች፣ ሬስቶራንቶች እና የንግድ ሱቆች በቋሚነት በሺዎች ሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥረዋል። ከአካባቢው የኮሪደር ልማት ጋር ተሳስረው የሚሰሩ የኢኮ ሪዞርቶችም ከተሞችን ይበልጥ ለጎብኝዎች ምቹ እያደረጉ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት እንደገለጹት የኮሪደር ልማት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ግቦች ያሉት ሲሆን ቋሚ የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ የዕውቀት ሽግግር ልምድን በመስጠት፣ ውብ የቤት ግንባታን በማሳለጥና አማራጭ መንገዶችን በመዘርጋት የትራፊክ መጨናነቅን በመቅረፍ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
በከተማ የኮሪደር ልማት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ቤት በመሥራት ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራቱንና አሮጌ ቤቶችን በማፍረስ ዘመናዊ አድርጎ በመሥራት የከተሞችን ገጽታ መቀየር መቻሉን ገልጸዋል።
ይህ የኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት በከተማ ብቻ ሳይወሰን ወደ አርሶ አደሮች ቀዬም የተሻገረ ሲሆን፣ በከተሞች የታየውን ለውጥ በማስቀጠል የገጠር የኮሪደር ልማትን በማፋጠን የአርሶ አደሮችን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር እየተሠራ ይገኛል።
በዚህም አርሶ አደሮች ዘመናዊ አኗኗርን እንዲላመዱ፣ ፅዱ የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸውና በንጽህና የሌማት ትሩፋትን (ከብት፣ ዶሮና ዕፅዋትን) እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
እንዲሁም መንገድ፣ መብራትና የቴሌኮም ዝርጋታዎችን እንዲያገኙ በማድረግ የገጠር እና የከተማ የንግድ ፍሰትን እጅግ ፈጣን እና ቀልጣፋ እንዲሆን አስችሏል።
በአጠቃላይ ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ሥራ በቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም መሥራት እንደሚቻልና በመተባበርና በቅንጅት መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ በተግባር ያሳየ የሀገራችን የብልጽግና ማሳያ ሆኗል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: