Search

የታንኩ እና የባንኩ አባዜ፡- ሲታቀፈው የሚመዘብረው፣ ሲርቀው የሚያፈነዳው ኋላ ቀሩ ቡድን

ማክሰኞ ነሐሴ 05, 2018 109

የኢትዮጵያን የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ታሪክ ወደኋላ መለስ ብሎ በጥልቀት ለሚቃኝ ማንም ሰው፣ የቡድኑ የ50 ዓመታት ጉዞ በአንድ ግልጽ መነጽር ሊታይ እና ሊመዘን ይችላል። ይህ ሚዛናዊ መነጽር "የታንክ እና የባንክ" ስሌት ነው። ይህ ኋላ ቀሩ የህወሓት ቡድን ታንኩንም ሆነ ባንኩን በአንድነት ሲታቀፍና ሲይዝ ብቻ የሚረጋጋ፣ ነገር ግን ከእነዚህ የስልጣን እና የሀብት ምንጮች ሲነጠልና ሲርቅ ደግሞ ኢትዮጵያን ወደማያባራ የረብሻ፣ የትርምስ እና የደም መፋሰስ አዘቅት ውስጥ የሚከት የጥፋት ኃይል ነው።

የዚህን ኋላ ቀር ቡድን እውነተኛ የፖለቲካ ባህሪ እና ማንነት ሁልጊዜም ቢሆን ላለፉት 50 ዓመታት ለመግለጽ፣ ከዚህ የተሻለ እና እውነታውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ትክክለኛ ቋንቋ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው።

ይህ ኋላ ቀሩ የህወሓት ቡድን ታንኩን (ወታደራዊ ኃይሉን) እና ባንኩን (የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት) አቅፎ በያዘበት ጊዜ፣ ሙሉ ትኩረቱ እና የዕለት ተዕለት ተግባሩ የሚሆነው የጥፋት ኔትወርኮቹን ማደራጀት፣ የኢትዮጵያ ሀብት ላይ መዝረፍ እና የራሱን ጠባብ የጥቅም ትስስር ማድለብ ላይ ብቻ ነው። በዚህ የስልጣን ዘመኑ ላሚቷ ኢትዮጵያን እንደ ላም ወስዶ ወተቷን እስከመጨረሻው ጠብታ እየማገ፣ የሀገራችን ማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ውስጥ ከቶ ወደ ኋላ አዘቅት ሲጎትታት ኖሯል።

ቡድኑ ይህን ታንክ እና ባንክ ማንም እንዳይነጥቀው ሲል፣ የተለያዩ የፖለቲካ ሴራዎችን በመሸረብ፣ ሕዝቦችን በመከፋፈል እና ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈነዱ የፖለቲካ የጊዜ ቦምቦችን በመቅበር ውድ ጊዜውን ሲያባክን ቆይቷል። ታንክ እና ባንክ በእጁ እስካለ ድረስ፣ ሀገራችንን እየመጠመጠ፣ እነዚህን የጥፋት ቦምቦች እየቀበረ አርፎ ይቀመጣል።

ነገር ግን፣ ልክ ከስልጣን መንበሩ ሲገፋ፣ ከታንኩም ከባንኩም ሲርቅ የቡድኑ ሌላኛው አስከፊ የጥፋት ገጽታ ይገለጣል። ከጥቅሙ ሲነጠል፣ ለዓመታት ያረገዛቸውንና ሲቀብራቸው የነበሩትን ፈንጂዎች አንድ በአንድ ማፈንዳት ይጀምራል። ኢትዮጵያ ለአንዲት ቀንም እንኳን እረፍት እንዳታገኝ ሌት ተቀን ይተጋል።

በ1967 ዓ.ም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለ17 ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያን እረፍት አልባ በሆነ የጦርነት እሳት ውስጥ እንድትዘልቅ ማድረጉ የዚሁ መገለጫ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከ2010 ዓ.ም የለውጥ ብርሃን መፈንጠቅ በኋላ፣ በየአካባቢው የፈጠራቸው ግጭቶች እና ያፈነዳቸው የጊዜ ቦምቦች ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያላደረገው ጥረት እንደሌለ በግልጽ ያሳያሉ።

የዚህ ኋላ ቀር ቡድን ብቸኛ መፍትሔ አድርጎ የሚያስበው ዳግም ወደ ስልጣን መመለስን ብቻ ነው። ሆኖም፣ ይህ በዚህ ትውልድ እና በዚህ እሳቤ ፈጽሞ ያበቃለት እና ያከተመ ትርክት ነው። አሁንም ቢሆን ይህንን ኋላ ቀር ቡድን ተሸክመው፣ እንደ "ትሮይ ፈረስ" በማገልገል ወደ ስልጣን ሊመልሱት የሚሞክሩ ኃይሎች አሉ። እነዚህ አካላት፣ ትናንት በኢህአዴግ የህገ-ወጥ የፖለቲካ ሥርዓት ስር ሲሰቃዩ፣ ሲበደሉ እና ሲታገሉ የነበሩ ቢሆንም፣ ዛሬ ግን ያንኑ ኋላ ቀር ቡድን መልሰው የተሸከሙ ናቸው።

በ1983 ዓ.ም እንዳደረጉት ሁሉ፣ ተሸክመው የስልጣን ኮርቻ ላይ ካወጡት በኋላ እንደካዳቸው ታሪክ እያወቀ፣ ዛሬም ከታሪክ መማር ተስኗቸው ትናንት የመታቸው ድንጋይ መልሶ እየመታቸው ያሉ አካላት ናቸው። ይህ እጅግ የከፋ ታሪካዊ ስህተት ነው።

በመጨረሻም፣ መታወቅ ያለበት ታሪካዊ ሀቅ ቢኖር፣ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ዳግም ኢህአዴግን የሚመልስ የፖለቲካ ሁኔታ ፈጽሞ አለመኖሩን ነው። የዚህ ኋላ ቀር ቡድን የፖለቲካ እሳቤ ሞቷል፣ ተቀብሯልም።

አዲሱ ትውልድ ይህንን የተቀበረ ሐሳብ ዳግም ለመቀበል የሚያስችል አንዳችም ፍላጎት የለውም። ይህ ኋላ ቀር ቡድን ታንክ እና ባንክ ታቅፎ ኢትዮጵያን የሚዘርፍበት፣ ሲያጣ ደግሞ የሚያተራምስበት ዘመን አክትሟል። ዳግም ወደ ስልጣን እመለሳለሁ ብሎ ማሰብም የተዘጋ ምዕራፍ እና ከንቱ ቅዠት ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: