ፖለቲካችን ላለፉት ዓመታት በጠላትነት እና ወዳጅ ትርክት የተሞላ፣ የሃሳብ ልዩነትን የማይቀበል እና ሁሉን ነገር በጡንቻ እና በአፈሙዝ እፈታለሁ የሚል የአሸናፊና ተሸናፊ አውድ የሆነ እጅግ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል የተጣባው ነው፡፡
እኔን ካልመሰለ ጠላቴ ነው ብሎ ፈርጆ የሚነሳ፣ እቡይነት የሞላበት፣ ወንድሙን የህልውና ስጋት አድርጎ በመፈረጅ ካራና ቃታ ሲማዘዝ የኖረ፣ አሁንም ድረስ የቀጠለ የብሽሽቅ፣ የአላካኪነት የትናንት ሁነቶች ላይ የተጣበቀ፣ ከመደጋገፍ ይልቅ የመጠፋፋት መንገድን የመረጠ አግድም አደግ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡
በእርግጥ በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ አስደናቂ የአብሮነት እና የሀገር ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ታሪክ ባለቤት ብንሆንም ቅሉ በዚሁ የተበላሸ የፖለቲካ ባህል ምክንያት በሌላው ገፅታው የእርስ በእርስ ግጭቶች እና ጦርነቶችን በወንድማማቾች መዕከል ስናደርግ የኖርን አሁንም ያለን ህዝቦች አድርጎናል፡፡
ጦርነት እና ግጭት ደግሞ በረከት አያመጣም፡፡ ጦርነት እና ግጭት ሀገራዊ ውድመት፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ መፈናቀል፣ እልቂቶተ፣ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ዘለቄታዊ የሥነልቦና ጠባሳዎች፣ ቁርሾ እና ቂምበቀሎች ይወለዳሉ፡፡
እነዚህ ለዘመናት ሲሸጋገሩ የመጡ የፖለቲካችን ውርሶች ናቸው ፖለቲካዊ ፅንፈኝነትን እየፈለፈሉ በብሔርና ጎሳ ካባ እየተሸፈኑ ዛሬም ድረስ ልጓም ላልተበጀለት ግጭቶች እና አለመግባባቶች መካረሮች እየዳረጉን ኖረዋል፡፡
እርስ በእርስ ተዋግተናል፣ ከጦርነት ምንም አላተረፍንም፣ አብዮት አካሂደናል፣ ከአብዮትም አንዳች አላገኘንም፤ ያልሞከርነው መንገድ ምክክር ብቻ ነበር፡፡
የለውጡ መንግሥት በእርግጥም የመውጫው መንገድ ሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትህን ማስፈን መሆኑን አፅንኦት በመስጠት በከፍተኛ ቁርተኝነት ይህንኑ እውን ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረው All-inclusive national dialogue ሁሉ አካታች የሆነ ሃገራዊ ምክክር በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ ያገኘው ታላቅ እድል ነው፡፡
ይህ ዕድል ሁሉንም አካላት ያሳተፈ አካታች የምክክር እድል ነው፡፡ በዚህ እድል ኢትዮጵያ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ይህ እድል የኖረውን የወንድማማችነት እሴት ያዳከመውን የተበላሸ የፖለቲካ ባህላችንን በማከም ዘላቂ ሰላማችንን ለማረጋገጥ፣በመሰረታዊ ጉዳዮቻችን ዙርያ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ እየዳበረ የሚሄድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ብሎም በመሃከላችን የእርስ በእርስ መተማመንን በመፍጠር የሕዝቦችን መተባበር እና አንድነት በማረጋገጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዚህ ነው በአንድ ወቅት "ጦርነትን ኖረንበታል። የተወሰኑ ችግሮቻችንን ፈትተንበታል፤ አብዮትን ደጋግመነዋል፤ የተወሰኑ ችግሮችን ፈትተንበታል፤ በሁለቱም ያልተፈቱትን ችግሮች ለመፍታት የቀረን መንገድ ምክክር ነው፤ ምክክርን ግን አልተጠቀምንበትም ጦርነትና አብዮት የተሟላ መፍትሔ የማያመጡት አሸናፊ እና ተሸናፊ ስለሚያስከትሉ ነው፤ በጦርነት ቢዘገይም የተሸነፈው ለማሸነፍ ይታገላል፤ ያሸነፈውም ድሉን ለመጠበቅ ይዋጋል፤ ምክክር ግን ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል፤ ከተሸነፍንም ሁላችንም ለሀገራችን ብለን ነው የምንሸነፈው" ሲሉ በትክክል የኢትዮጵያን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
"ይህ ትውልድ ያገኘውን መልካም ዕድል በቅንነት በመጠቀም የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ እንዲያንፅ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ!" ሲሉም ታሪካዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈው ነበር፡
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: