የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ሪፎርም ማድረግ ያስፈለገው ከግሎባላይዜሽንና ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ እየመጠቀ የመጣውን ድንበር ዘለል ወንጀል ለመከላከል እና ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የፖሊስ ኃይል ለመገንባት ነው።
ከዚህ ቀደም ተቋሙ የሎጅስቲክስ አቅም ከመጠቀም አንፃር ክፍተቶች የነበሩበት ሲሆን፣ አሁን ግን ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ የላቀ እና ዘመናዊ አሰራርን የተላበሰ ፕሮፌሽናል ሰራዊት ማፍራትን ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ ተነስቷል።
የፖሊስ ሠራዊቱን ኑሮ በማሻሻል እና ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር ሁልጊዜም ለህዝብና ለሀገር ጸጥታ ዝግጁ የሆነ የፖሊስ ሰራዊት መፍጠር ተችሏል።
ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ተቋሙ ከኋላ ቀር አሰራር በመውጣት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ አስተዳደር የታነጸ ኃይል መሆን ችሏል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ አንስቶ "በጀግንነት መጠበቅ፣ በሰብዓዊነት ማገልገል" የሚለው መሪ ቃል በሰራዊቱ የየዕለት ህይወት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሰርጿል።
የሰራዊቱ ሙያዊ ብቃት ማደግና ሌብነትን እንዲሁም ብልሹ አሰራርን አምርሮ መታገሉ በህዝብ ዘንድ ያለውን ክብር፣ ፍቅር እና እምነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድም በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው "ሰው አልባ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ" በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ መጀመሩ የተቋሙን የላቀ የዕድገት ከፍታ ያሳያል።
በተጨማሪም የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ እና የ991 ነፃ የስልክ መስመር የፖሊስን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ አድርገውታል።
የኃይል አጠቃቀም በሕጋዊነት፣ በተመጣጣኝነትና በጥብቅ ተጠያቂነት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገባ በመደረጉ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዲወገድ እና ወንጀል ምርመራው በዘመናዊ ቴክኒካዊ አቅም እንዲታገዝ አስችሏል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በማስተማር ላይ ይገኛል። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሎጅስቲክስ፣ የሰው ኃይል እና የትጥቅ አቅሙን በማጎልበት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በሰላም ከማስተናገድ አልፎ በአፍሪካ አርአያ የሚሆን ሞዴል የጸጥታ ተቋም ለመሆን በቅቷል።
ይህ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት በመንግስት የቅርብ ክትትል፣ በከፍተኛ አመራሩ ቁርጠኝነት እና በሠራዊቱ ጀግንነት የተመዘገበ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: