በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረጅም ዘመን የቆዩ ቅራኔዎች እና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ሲንከባለሉ መቆየታቸው አይካድም። እነዚህን ቅራኔዎች በጦርነትና በኃይል ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች ዘላቂ ሰላም ማምጣት ባለመቻላቸው ከቀውሱ አዙሪት መውጣት አልቻልንም፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ትልቅ ሀገራዊ ተስፋን የሰነቀ ነው።
ከምንም በላይ ይህ ሂደት የፖለቲካ ባህላችን በከፍተኛ ደረጃ መቀየሩን በግልጽ የሚያሳይ ነው። የኃይል ፖለቲካን ወደ ጎን በመተው በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ መደማመጥ መጀመራችን፣ እንዲሁም በልዩነት ውስጥ ሆነው ሐሳብ ለሐሳብ መሞገታችን ሲታይ መመካከሩ በራሱ እንደ አንድ ትልቅና ታሪካዊ ውጤት የሚቆጠር ድል ነው።
ይህ ታላቅ መድረክ ከመነሻው እስከ መድረሻው ፍፁም የኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል። የሀገር ጉዳይ ይመለከተኛል፣ ያገባኛል ያሉ ከሁሉም የሀገራችን ማዕዘናት የተውጣጡ ተወካዮች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰባስበው የጋራ ቤታቸውን እጣ ፈንታ እርስ በእርስ እየተመካከሩበት ነው።
ሁሉም ተመካካሪ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት፣ በራሱ ቋንቋና ባህል ሙሉ ነፃነት ተሰጥቶት ስጋቱን እና ምኞቱን እያንፀባረቀ መሆኑ ችግሮቻችንን በራሳችን አቅምና በሰከነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያስመሰክር ነው።
ጉባኤው ዛሬ አዳራሽ ውስጥ ለደረሰው ታሪካዊ ውይይት የበቃው እጅግ ሰፊ፣ አድካሚና አካታችነትን ማዕከል ያደረገ ረጅም ሂደት አልፎ ነው። ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት በ1 ሺህ 195 ወረዳዎች በመንቀሳቀስ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አርሶና አርብቶ አደሮችን፣ መምህራንን፣ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ድምፅ የማሰባሰብና ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራ በጥራት ሠርቷል።
ከሀገር ውስጥ አልፎም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሳይቀሩ አጀንዳቸውን የሚያስይዙበት ሰፊ እድል የተመቻቸበት ፍፁም አቃፊ ሂደት ነበር።
በዚህ እጅግ አካታችና ሰፊ ከሆነው ሕዝባዊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በኋላ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ ጥልቅ ውይይትና ምክክር እንዲደረግባቸው ተብለው ስምንት የተደራጁ አጀንዳዎች ተለይተው ቀርበዋል። እነዚህ ስምንት አጀንዳዎች የሕዝቡን ስጋት፣ የዘመናት ቅሬታዎችና የሀገራችንን አንገብጋቢ ጉዳዮች መሰረት አድርገው የተደራጁ በመሆናቸው፣ ተመካካሪዎቹ በእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይተው የጋራ ምክረ ሐሳብ ያስቀምጣሉ፡፡
በዚህ ታሪካዊ የምክክር ጉባኤ ሂደት ውስጥ በግልጽ መታወቅ ያለበትና ብዙዎች ሊገነዘቡት የሚገባው ዋነኛ ነጥብ፣ የምክክሩ መጨረሻ በቀጥታ ውሳኔ ማሳለፍ አለመሆኑን ነው። ጉባኤው የህግ አውጪነት ወይም የአስፈፃሚነት ስልጣን ተሰጥቶት የመጨረሻ ውሳኔ የሚያሳልፍ አካል ሳይሆን፣ ተወካዮቹ በስምንቱ አጀንዳዎች ላይ በጋራ በመመካከርና መግባባት ላይ በመድረስ ለሀገር አስተማማኝ መፍትሔ የሚሆኑ ዘላቂ ምክረ-ሐሳቦችን የሚያመነጩበት መድረክ ነው።
እነዚህ ከሕዝብ የፈለቁና በውይይት የዳበሩ ምክረ-ሐሳቦች በመጨረሻም ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት ቀርበው ወደ ፖሊሲና ትግበራ እንዲቀየሩ የሚደረግ ይሆናል። ይህ አካሄድ ለዘመናት ሲያጋጩን የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት፣ በሕዝብ አመኔታ የተገነባ ጠንካራና አካታች ሀገረ-መንግሥት ለመፍጠር ፅኑ መሰረት ይጥላል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: