Search

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሉዓላዊነት ጥበቃ እስከ የሀገር እድገት ዋስትና

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 109

የአንድ ሀገር ኅልውና፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝቦች ማኅበራዊ ፋይዳ መሠረቱ አስተማማኝ ሰላም እና ፀጥታ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን የድንበርና ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባሻገር፣ የሕዝቦቿን ሰላም የሚያስጠብቅ፣ የነገ ተስፋን የሚያረጋግጥ እና ሀገራዊ ኅልውናን የሚያፅና ዋና ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

ሠራዊቱ የሀገር ውስጥ ሰላምን በማስከበር እና በማፅናት የሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚተጋ ውድ ሕይወቱንም መስዋዕት የሚያደርግ የሕዝብና የሀገር ውድ ጋሻ ነው።

ሰላም ደግሞ እንዲሁ በምኞት የሚገኝ ሳይሆን፣ በፅኑ ትጋትና በከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠበቅ ሀብት ነው። የመከላከያ ሠራዊታችን ይህንን እውነት በመገንዘብ የሀገርን ድንበርና ሉዓላዊነት በማስከበር የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና የመኖር መብት ያረጋግጣል።

አብሮነትና ወንድማማችነት በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም በማድረግ ስጋቶችን አስቀድሞ ይከላከላል። ከማንኛውም ወገንተኝነት ነፃ በመሆን የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ብቻ አንግቦ በመንቀሳቀስ የሀገር ኩራትና አለኝታ መሆን ችሏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሰላም ከማስከበር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ የሰላም አምባሳደር ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በመሆን በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ ያከናወናቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የሠራዊቱን ከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ-ምግባር እና ሙያዊ ብቃት ያስመሰከሩ ናቸው።

ይህ አህጉራዊ አስተዋፅኦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ እና የታማኝነት ደረጃ ከፍ እንዲልም አድርጎታል።

ልማትና ብልፅግና ያለ ሰላም ሊታሰቡ አይችሉም። ሠራዊቱ የፀጥታ ግዴታውን ከመወጣት ባሻገር ሀገር ወደተሻለ የኢኮኖሚ ምዕራፍ እንድትሸጋገር የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

በዚህም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የባቡር መስመሮች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የልማት እንቅስቃሴያቸው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲከናወኑ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ነው።

አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ በመፍጠር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ትልቅ ድርሻ በመጫወት እንዲሁም በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ፈጣን ድጋፍ በመስጠት የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ታድጓል።

በአረንጓዴ ዐሻራና በሀገራዊ የልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊም ነው። በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አቅም፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንና የአየር ኃይል ብቃት በማደራጀት ራሱን በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስና ስልጠና እያበቃ ይገኛል። ይህም የሀገርን የደኅንነት ስጋቶች አስቀድሞ የመከላከልና የመመከት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ግልፅና ጥብቅ ነው። ሰላምን ማስከበር፣ ሰላምን ማፅናት፣ ሰላምን መጠበቅ እና የሀገር ብልፅግና ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ማድረግ።

ይህም ሀገራችን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ቆማ ወደ ተሻለ የስልጣኔ እና የብልፅግና ማዕረግ እንድትሸጋገር የሚያስችል ዋና መሠረት ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: