የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሲታሰብ አብዛኛው ሰው ህሊና ውስጥ የሚመጣው ችግኝ የመትከልና የተጎዱ መሬቶችን የመንከባከብ ተግባር ነው። ነገር ግን፣ በስትራቴጂካዊ የይዘት እይታና በሀገራዊ የልማት መስመር ስንመረምረው፣ አረንጓዴ ዐሻራ ዛፍ ተክሎ የማሳደግ ሥራ ብቻ አይደለም።
ይልቁንም የሀገራችንን የኃይል አቅርቦት፣ የኢንዱስትሪ ዕድገት እና የሰው ኃይል ክህሎት በአንድ ላይ የሚያስተሳስር ሁለገብ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክት ነው።
ይህ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ቀጣናዊ አቅምን ለመገንባት በምታደርገው ጉዞ ውስጥ ትልቁን ሚና ይጫወታል። በዚህም የአፈር መሸርሸርን እና ደለል ወደ ታላላቅ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦች እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዳይገባ ይከላከላል።
ይህም የኃይል ማመንጫ አቅምን በማጎልበት የአገልግሎት ዘመናቸውን ያራዝማል። በመርሐ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞች የደን ሽፋንን በመጨመር፣ የከባቢ አየር እርጥበትን በመጠበቅና የከርሰ ምድር ውሃን በማበልጸግ የማቋረጥ ባህሪ የሌለው ታዳሽ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋሉ።
የኢንዱስትሪ ዘርፉ ውጤታማነት በቀጥታ ከጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ከዘላቂ የካርቦን ልቀት ቅነሳ ፖሊሲዎች ጋር የተያያዘ ነው። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሚተከሉ የተቀናጁ የፍራፍሬ፣ የእንጨትና የንግድ ሰብሎች ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ የጥሬ ዕቃ ምንጭ እየሆኑ ይገኛሉ።
የዓለም አቀፍ ገበያ ወደ አረንጓዴ ምርቶች እየተቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በዘላቂ መንገድ ከተጠበቀ አካባቢ የሚገኙ ምርቶች በውጭ ገበያ ተወዳዳሪነታቸው የጎላ ነው።
ኢንዱስትሪዎችም በድርቅ፣ በጎርፍና በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሚደርስባቸውን የፋይናንስና የሥራ ማቋረጥ አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።
አረንጓዴ ዐሻራ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በተለይም ወጣቶችን የሚያንቀሳቅስ ትልቅ የትምህርትና የክህሎት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
ማኅበረሰቡ ከባህላዊ የችግኝ ተከላ አልፎ ዘመናዊ የችግኝ ማፍላት፣ የተክሎች እንክብካቤ፣ የዘላቂ አፈርና ውሃ ጥበቃ ቴክኒኮችን እንዲለምድ አድርጓል።
በችግኝ ማፍላት፣ በምርምር፣ በደን ጥበቃና ተያያዥ የሥራ ዘርፎች ላይ ለብዙዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የፈጠራና የኢንተርፕሪነርሺፕ አስተሳሰብን እየገነባ ይገኛል።
የአመለካከትና የባህል ለውጥ በማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን እንደ ሀገራዊ ግዴታና የኢኮኖሚ መሰረት አድርጎ የመውሰድ አዲስ የማኅበረሰብ ባህል እንዲገነባ አስችሏል።
በመሆኑም አረንጓዴ ዐሻራ ከተፈጥሮ ጥበቃ ባለፈ የኢትዮጵያ የወደፊት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እድገት መሠረት እየሆነ ይገኛል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: