Search

በባህር ዳር ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን የቤት ባለቤት የሚያደርገው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እጣ የማወጣት መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 296

የመደመር መንግሥት እየተገበራቸው ካሉ ሰው ተኮር ተግባራት መካከል የዜጎችን የቤት መስሪያ ቦታ አቅርቦት ችግር መፍታት ቀዳሚው ተግባር አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደርም በመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበር ለተደራጁ የቤት ማህበራት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የብሎክ ዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር በዛሬው እለት እያካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ ባህርዳር ከተማን ለሰው ልጆች የተመቸች ከተማ ለማድረግ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፣ በዛሬው እለትም አስፈላጊውን መረጃ ያሟሉና ህጋዊ መሠረት ያላቸው 901 ማህበራት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ይፋ ባደረገው የብሎክ እጣ መሠረት በአራት ሳይቶች ማለትም ወረብ፣ አዲስ ዓለም፣ መኮድ እና ሰልቸን በተባሉ 1045 ሄክታር መሬት ላይ ቦታዎቹ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋል።

በዚህም ህጋዊ መሥፈርቶችን ያሟሉት 901 ማኅበራት ውስጥ የሚገኙ 19 ሺህ 698 አባላት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በቀጣይም በባህርዳር ከተማ የሚስተዋለውን የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ሓላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የክልሉ መንግስት የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማሟላት የተለያዩ አማራጮችን ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዜጎችን የቤት ባለቤት በማድረግ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተጋ ያለው የለውጡ መንግስት፣ የቤት ልማት ፖሊሲ ዘርግቶ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት በክልሉ ከ140 ሺህ በላይ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የቤት ባለቤት መሆናቸውን ሀላፊው አስረድተዋል።

በተስፋሁን ደስታ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: