በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ እመርታ የተረጂነት አስተሳሰብን በመስበር ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የታሪክና የምርታማነት ምዕራፍ እያሸጋገራት መሆኑን የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽነሩ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ በመከላከልና አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል የአሰራርና የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል።
ይህ ታሪካዊ እርምጃ ዜጎችን ከተረጂነት አመለካከት በማላቀቅ የአደጋ ተጋላጭነትንና የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በጥቅሉ መቀነስ አስችሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ተነሳሽነት የተረጂነትን አስተሳሰብ የሰበረ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ሽፈራው፣ በዓለም አቀፍ አጋሮች ላይ የተመረኮዘውንና አስተማማኝ ያልነበረውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በራስ አቅም ለመተካት በተከናወነው ሥራ ትልቅ የታሪክ ለውጥ መመዝገቡን አብራርተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲን በማውጣት፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን በመከለስ ዜጎችን ከተረጂነት ነፃ ለማድረግ በትኩረት ተሰርቷል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ክብር ከማስጠበቅ ባሻገር ነፃነትንና የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሰረት እየጣለ ይገኛል። ለዚህም ስኬት የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ተቋቁሞ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተደረገው የተቀናጀ ጥረትና በኢኮኖሚው ዘርፍ በተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 27 ሚሊዮን በ2018 ዓ.ም ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የክልሎች አቅም እያደገ በመምጣቱ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን በራሳቸው መሸፈን መጀመራቸውን ተናግረዋል። የሎጂስቲክስና የማከማቻ መጋዘኖችን ሥርዓት በማጠናከር፣ እስከ ታችኛው የመዋቅር ደረጃ የመጠባበቂያ ክምችት በመዘርጋት ለዜጎች አስተማማኝ ዋስትና እየተፈጠረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ አደጋዎች ሲያጋጥሟት ከውጭ ሀገራት ይጠየቅ የነበረውን ድጋፍ በመቀነስ አዲስ የማንሰራራት ዘመን እያበሰረች መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ሽፈራው፣ አሁን እየተገነባ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ ሥርዓት ከራስ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚተርፍ ልምድ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: