Search

ከፓሪስ ጎዳናዎች እስከ ጣና ሞገድ ሳዑዲያዊውን ቱሪስት ያስደመመችው የባሕር ዳር አዲሷ ገጽታ

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 151

በተፈጥሮ ጸጋ የታደለችውና የጣና ሀይቅ ፈርጥ የሆነችው ውቧ የባሕር ዳር ከተማ፣ በአረንጓዴ ልምላሜዋና በማራኪ ገጽታዋ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደምቃ ትታያለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለከተሞች ልማት የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ ተስፋዋ የለመለመው ይህች ማራኪ ከተማ፣ ራሷን በፍጥነት በማደስ ላይ ስትሆን፣ በተለይም አዲስ የተገነባው የጣና ድልድይ ለከተማዋ ልዩ ግርማ ሞገስን አላብሷታል።

ቀደም ሲል በሀይቁ ዙሪያ በዘፈቀደ ተገንብተው የነበሩና በቂ አገልግሎት የማይሰጡ መሠረተ-ልማቶች፣ በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ጠብቀው በድጋሚ በመገንባታቸው የቱሪስቶችን ቀልብ በከፍተኛ ሁኔታ እየሳቡ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተጠቅሞ ወደዚች ከተማ ያቀናው ታዋቂው ሳዑዲያዊ የጉዞ ቪዲዮ ይዘት አዘጋጅ አሊ ዳውድ፣ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በጣና ሀይቅ ዙሪያ ያለውን አስደናቂ ተፈጥሮ በካሜራው ሌንስ እያጣጣመ ይገኛል።

በሞተር ጀልባ የጣናን ሞገድ እየሰነጠቀ፣ በከተማዋ መሐል በምሽት በእግሩ እየተጓዘ የባሕር ዳርን ነፋሻማና ጤናማ አየር መማግ ልዩ የውስጥ እርጋታን እንደፈጠረለት በግርምት ይመሰክራል።

ሀይቁ ለከተማዋ ትልቅ ገጸ-በረከት መሆኑን የሚያነሳው አሊ፣ በዙሪያው የተገነቡት ዘመናዊ ሆቴሎችና ሎጆች የጣናን ውበት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ ማድረጋቸውን ገልጾ፣ ከጣና ሀይቅ የሚወጣውን ጣፋጭ ዓሳ እየተመገበና የሀይቁን ግዝፈት እያደነቀ የማይረሳ የጉዞ ትዝታን ሰንቋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችው ባሕር ዳር በኮሪደር ልማት ሰፋፊ የእግረኛ፣ የሳይክልና የተሽከርካሪ መንገዶች ተገንብተውላት አዲስ መንፈስ የተላበሰች ሲሆን፣ ይህ አርአያነት ያለው የልማት ሥራ ወደ ጎርጎራ ሎጅ፣ የፋሲለደስ ቤተ-መንግሥት እድሳትና የጎንደር ከተማ ኮሪደር ልማት በመስፋፋት ላይ ይገኛል።

ቱሪዝምና የጉዞ ቪዲዮዎችን በመቅረጽ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያጋራው አሊ ዳውድ፣ ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ የሰለጠኑ የአውሮፓ ሀገራትን የጎበኘ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ሲደርስ የተሰማው ስሜትና ያገኘው አቀባበል ግን እጅግ የተለየና ልዩ ሆኖ እንዳገኘው በደስታ ይገልጻል።

የተፈጥሮ ቱሪዝም መዳረሻዎችን አጥብቆ የሚወደው ይህ ቱሪስት፤ ባሕር ዳርን፣ ቤኑናን፣ ወንጪን፣ ቢሾፍቱንና የእንጦጦ ፓርኮችን በመጎብኘት ያገኘውን ወደር የለሽ ደስታ በካሜራው ለዓለም ያጋራ ሲሆን፣ በቀጣይም ይህንን ድንቅ አገር መላ ቤተሰቡን ይዞ ዳግም ለመጎብኘት ቃል ገብቷል።

የባሕር ዳር አዲሷ ገጽታና የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋ በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች እይታ ውስጥ ገብቶ አዲስ የቱሪዝም ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: