Search

ሀገራዊ ምክክር፡ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ተስፋ

ዓርብ ነሐሴ 08, 2018 325

በሀገራችን እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አብረው መቀመጥ እና መመካከር መቻላቸው በራሱ ትልቅ ሀገራዊና ታሪካዊ ዋጋ ያለው እርምጃ ነው።

ይህ የጋራ መድረክ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው እጅ መወሰን የጀመሩበት ብሩህ አጋጣሚ ነው።

ለዘመናት ተከማችተው መፍትሔ ያላገኙ ልዩነቶችን፣ ቅሬታዎችን እና ፈተናዎችን በኃይል ሳይሆን በውይይት ለመፍታት በጋራ መቀመጥ መቻላችን ኢትዮጵያ ወደሰለጠነ እና ዘላቂ ሰላም ወዳለው ምዕራፍ እያደረገች ያለውን ተስፋ ሰጪ ጉዞ ያበሥራል።

ውይይት የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ በመሆኑ በራሱ የታላቁ መፍትሔ መጀመሪያ እና ዋና መድረክ ነው።

የዚህ የምክክር ሂደት ልዩ ውበት እና ጥንካሬ የተለያዩ አመለካከቶች፣ የፖለቲካ ፍላጎቶች እና ማኅበራዊ መሠረቶች ያላቸው አካላት በአንድ ማዕድ ላይ መገናኘታቸው ነው።

ቀደም ሲል የማይደማመጡ እና የማይነጋገሩ አካላት በአንድ ላይ ተሰብስበው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መቻላቸው ልዩነቶችን ለማጥበብ እና የጋራ ግንዛቤን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

ይህ እውነታ ለትውልድ የሚሻገር የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ መሠረት ነው።

ይህ የባለድርሻ አካላት የሰለጠነ ውይይት እና የሃሳብ ፍሰት ሀገራዊ አንድነት እና መከባበርን በጠንካራ አለት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የሚደመጡ ድምፆች ሁሉ እኩል ዋጋ አላቸው። ብሔር፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት ወይም ማኅበራዊ ደረጃ ሳይለያያቸው የሁሉም ዜጋ እና አካል ድምፅ እኩል የሚደመጥበት አሠራር መኖሩ፣ የሂደቱን ሕጋዊነት እና ተቀባይነት አስተማማኝ ያደርገዋል።

ማንም የበላይ ወይም የበታች ሳይሆን፣ ሁሉም እኩል ባለቤት የሆነበት የምክክር ምኅዳር መፈጠሩ ለፍትሐዊ እና አሳታፊ ውሳኔዎች መንገዱን ጠርጓል።

ከሁሉም በላይ ግን የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ምክክር እምብርት እና ማዕከል ኢትዮጵያ ናት። የሁሉም አካላት ሃሳብ፣ ክርክር እና ፍላጎት የመጨረሻ ግብ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ዘላቂ ሰላም፣ ፍትሕ እና ብልፅግና ማረጋገጥ ነው።

የግል እና የቡድን ፍላጎቶች ከሀገር ዘላቂ ሕልውና እና ከሕዝብ ጥቅም በታች ሆነው የጋራ ሀገራችንን የተሻለች እና ጠንካራ አድርጎ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ማዕከል ሆና ትቀጥላለች።

በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ለዚህ ሀገራዊ የውይይት መድረክ ስኬት የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ሊጫወት ይገባል።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: