የመደመር መንግሥት የልማት እና የብልጽግና ጉዞ የሚጀምረው ረቂቅ ከሆነ የሐሳብ ጽንስ ነው። እያንዳንዱ ታላቅ ሀገራዊ ስኬት፣ የረጅም ዘመን ራዕይ እና የትውልድ ሽግግር መነሻው የጠራ ሐሳብ ነው።
ሐሳብ ዘር ናት፤ በአግባቡ ሲጸነስ፣ ሲዘራ፣ በላብ ሲኮተኮት እና ተገቢውን እንክብካቤ ሲያገኝ የትውልድን ረኃብ የሚያስታግስ እና ሀገርን ከፍታ ላይ የሚያስቀምጥ ግዙፍ የተግባር ፍሬ ያፈራል።
የመደመር ፍልስፍና የውጭውን ዓለም ርዕዮተ ዓለም በጭፍን ከመገልበጥ እና ከመጠቀም ይልቅ፣ ስለ ኢትዮጵያ እምቅ አቅም እና ጸጋ በጥልቀት በማሰብ እና በማሰላሰል የተጠነሰሰ የሐሳብ ዘር ነው።
ይህ አዲሱ የሀገረ መንግሥት አስተሳሰብ በግብታዊነት እና በዘፈቀደ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን፣ አርቆ የሚያስብ፣ በጥልቀት የተነደፈ፣ በሚገባ የታቀደ እና የተለካ እርምጃ የሚራመድ ሥልጡን ተቋም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል። እውነተኛ ሀገር ወዳድነት በቃላት ዲስኩር ብቻ ሳይሆን በቁርጠኝነት በሚመራ የልማት ሥራ የሚገለጽ መሆኑን የመደመር መንግሥት የዕለት ተዕለት የፖለቲካና የኢኮኖሚ መርሕ አድርጎታል።
የመደመር መንግሥት የሐሳብ ዘርን ወደ ተግባር ፍሬ የመቀየር ሒደት፣ ተከታታይነት እና ተያያዥነት ያለው፣ ከትንሽ ተነሥቶ ወደ ግዙፍ ሀገራዊ ሥዕል የሚያድግ የለውጥ ፓተርንን ይከተላል።
ይህ እየሰፋ የሚሄድ የዕድገት እና የለውጥ ጂኦሜትሪ በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ በተሠሩ ሥራዎች ቁልጭ ብሎ ይታያል። የለውጡ ጅማሬ እንደ አንድ የሐሳብ ማሳያ ከተወሰደው ማዕከል፣ ከቤተ መንግሥት ግቢ (ከአንድነት ፓርክ) አንሠራራ።
ያቺ በግቢ ደረጃ የተዘራችው የለውጥ ዘር አድማሷን በማስፋት "ገበታ ለሸገር" በሚል አዲስ አበባን ወደ ውብ የቱሪዝም ማዕከልነት ቀየረች።
የከተማዋን ገጽታ ያደሱት የሸገር ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ ዘመናዊ የኮሪደር ልማቶች እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች የዚህ ስኬት ሕያው ማሳያዎች ናቸው። ይህ እየሰፋ የሚሄድ የለውጥ ጉልበት በዋና ከተማዋ ብቻ ሳይገደብ፣ "ገበታ ለሀገር" በሚል ሀገራዊ ማዕቀፍ ወደ ክልሎች ተሻግሮ ወንጪን፣ ኮይሻን እና ጎርጎራን ወደ ማራኪ የቱሪስት መዳረሻነት ቀይሯል።
የለውጡ ማዕበል በዚህም ሳያቆም "ገበታ ለትውልድ" በሚል መሪ ሐሳብ የነገውን ትውልድ ተጠቃሚነት ወዳረጋገጠ፣ በርካታ ዞኖችን እና ክልሎችን ወደሚያስተሣሥር ሀገራዊ የቱሪዝም አብዮት ከፍ ብሏል።
ሐሳብ ከቤተ መንግሥት ተነሥቶ መላ ሀገራችብን ያዳረሰበት ይህ የለውጥ አድማስ፣ የመደመር መንግሥት ሥራዎች እርስ በርስ የተሣሠሩ እና በሒደት ያደጉ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ይህ ተከታታይነት ያለው የልማት ዝላይ እንዲሁ በአጋጣሚ የተፈጠረ ክስተት አይደለም።
የሀገራችን የለውጥ አመራር ከዚህ ቀደም እንዳስገነዘበው፣ ዛሬ በየቦታው የምናስቀምጣቸው ትናንሽ ነጠብጣቦች (Dots) ወይም የልማት ሥራዎች፣ ነገ ጊዜያቸውን ጠብቀው ሲገጣጠሙ አንድ ላይ ሆነው የሚፈጥሩት ግዙፍ ሀገራዊ ምስል አለ።
አሁን በየአካባቢው የሚታየው እያንዳንዱ የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻ እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለብቻው ተነጥሎ ሲታይ ትክክለኛው ትልቅ ምሥል ወዲያውኑ ላይታይ ይችላል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ግን እነዚህ ነጠብጣቦች ሲገጥሙ እና ሲገናኙ የሚፈጥሩት ግዙፍ የብልጽግና ሥዕል አለ።
በመደመር መንግሥት የሐሳብ ማኅደር ውስጥ ይህ ትልቁ ምሥል ቀድሞውኑ በምናብ የተሣለ እና የተነደፈ ነው። ነጠብጣቦቹ ሲገናኙ የኢትዮጵያን ሙሉ የብልጽግና እና የውበት ሥዕል ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ይህ ነው እንግዲህ መንግሥትን የጸና፣ ምክንያታዊ እና እጅግ ተራማጅ የሚያደርገው።
በመደመር ፍልስፍና መነጽር፣ ኢትዮጵያን እወዳለሁ ማለት ኢትዮጵያን ማልማት፣ መሥራት እና በተግባር መቀየር ማለት ነው። የሀገር ፍቅር የሚገለጸው ቁጭ ብሎ በመመኘት ሳይሆን፣ አዕምሮን አሠርቶ የሐሳብን ጽንስ በመቅረጽ፣ በተቀናጀ ዕቅድ በመምራት እና ሌት ተቀን ታግሎ የተግባር ፍሬውን በማጨድ ነው።
ይህ ፍልስፍናዊ አቋም የመደመር መንግሥት ሁልጊዜም ስለ ኢትዮጵያ ከፍታ የሚያስብ፣ የፈጠራ አቅሙን ያጎለበተ እና የዜጎችን ኑሮ በተጨባጭ ለመለወጥ የሚተጋ መሆኑን ያረጋግጣል። ሐሳብ ወደ ተግባር ሲለወጥ ሀገር ትቀየራለች። የቱሪዝሙ ዘርፍ የዚህ የተግባር ፍልስፍና አንዱ ደማቅ ማሳያ ሲሆን፤ ዛሬ የተዘሩት የቱሪዝም፣ የኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ዘሮች ነገ ለትውልድ የሚተርፍ ታላቅ የኢኮኖሚና የሥልጣኔ ፍሬ ሆነው ሀገራችንን ወደ አፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነት እንደሚያሸጋግሯት ጥርጥር የለውም።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: