የጉዞ ከረጢታችንን አንግበን ወደተለያዩ የሀገራችን ማዕዘናት ስንጓዝ፣ አብዛኛውን ጊዜ አይኖቻችን የሚያርፉት በፈጣሪ ጥበብ በተንቆጠቆጡ ውብ ተፈጥሮዎች፣ ዘመናትን በተሻገሩ ታሪካዊ ቅርሶች እና ማራኪ የመዳረሻ ስፍራዎች ላይ ነው።
ነገር ግን በእነዚህ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበቶች እና መስህቦች መሃል ስናልፍ፣ ከዕይታ ባሻገር የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በተግባር የሚለውጥ እና የኢኮኖሚ ህይወትን በአዲስ መልክ የሚያለመልም ግዙፍ የገበያ አውታር እናገኛለን።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ መስፋፋት ከተራ የመዝናኛ ጉዞ ወሰን አልፎ በአካባቢው ለሚኖሩ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች እና አነስተኛ አምራቾች አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ከፍቷል።
የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ልዩ ልዩ የመዳረሻ ስፍራዎች በስፋት ማቅናት ሲጀምሩ፣ በመንገዳቸው ላይ ትልቁ ፍላጎታቸው የሚያርፈው በአካባቢው በሚመረቱ ትኩስ የምግብ እና የግብርና ምርቶች ላይ ነው።
ይህ አስደሳች አጋጣሚ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ያለ ምንም ደላላ ጣልቃ ገብነት እና አድካሚ የትራንስፖርት እንግልት ምርቶቻቸውን በደጃቸው የሚሸጡበትን ሰፊ የገበያ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
በየመስህብ ስፍራዎቹ የሚታየው የቱሪስቶች ፍሰት የገበያ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር፣ የአርሶ አደሩን የአመራረት ዘይቤ እና የገቢ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው ይገኛል።
ቱሪስቶችን የሚያስተናግዱ ሆቴሎችና ሎጆች ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን አጥብቀው ስለሚፈልጉ፣ አርሶ አደሩ አሰራሩን በማዘመን በጥራት ላይ ይበልጥ እንዲያተኩር አድርጎታል።
ከዚህም ባሻገር በጉዞ መስመሮች ላይ በእርሻ ስራ እና በጥቃቅን ንግድ ላይ የተሰማሩ የአካባቢው ሴቶች እና ወጣቶች፣ የቱሪስቶችን ፍላጎት ተጠቅመው የራሳቸውን ንግድ በማስፋፋት በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን ችለዋል።
ቱሪዝም የተፈጥሮ እና የታሪክ ውበቶቻችንን ለዓለም ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ የዜጎችን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ጥራት የሚያሻሽል ዘላቂ የህይወት ትስስር ነው።
በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የገበያ ድልድይ በማጠናከር የሀገር ውስጥ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ሞተር የሚያሽከረክር ታላቅ ኃይል ነው።
የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበት ለአርሶ አደሩ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ በመሆን፣ የቱሪስቶች መብዛት የገበያ በሮችን በሰፊው በመክፈት የዜጎችን የኢኮኖሚ ህይወት በተግባር የሚያቀና ውድ ብሔራዊ ሀብታችን መሆኑን በእያንዳንዱ ጉዟችን ላይ እንታዘባለን።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: