Search

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ያዘጋጀው ልዩ አገልግሎትና የ50 ቢሊዮን ብር የብድር ማዕቀፍ ይፋ ተደረገ

ቅዳሜ ነሐሴ 09, 2018 135

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡ የዳያስፖራ አባላት የተሻለና ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ራሱን የቻለ ክፍል አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ።

 

የባንኩ የሪቴይል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ አለሙ ከዳያስፖራ አባላት ጋር ባደረጉት የውይይት መድረክ እንዳብራሩት፣ ተቋሙ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚውል ዓመታዊ የ50 ቢሊዮን ብር የብድር ማዕቀፍ በልዩ ሁኔታ መድቧል።

ይህ ሰፊ የብድር አገልግሎት በመደበኛው እና በሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ በተመጣጣኝ የወለድ ምጣኔ የሚሰጥ ሲሆን፣ ደንበኞች እንደየፍላጎታቸው ብድሩን በብር ወይም በውጭ ምንዛሪ መመለስ የሚችሉበት ምቹ አሰራርም ተዘርግቷል።

ከብድር አገልግሎቱ ባሻገር በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በቀላሉ ገንዘብ መላክ እንዲችሉ እንደ ሲቢኢ ኮኔክት (CBE Connect) እና ኢትዮዳይሬክት (EthioDirect) ያሉ ዘመናዊ ዲጂታል አማራጮች መዘጋጀታቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ  ገልጸዋል።

በተጨማሪም የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል በተዘጋጀው 'unite.et' የተሰኘ አዲስ ዲጂታል መተግበሪያ፣ በሚኖሩበት ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች፣ በህጋዊ ወኪሎቻቸው ወይም ወደ ሀገር ሲመጡ በአካል በመገኘት በቀላሉ የባንክ ሂሳብ መክፈት እንደሚችሉ በውይይቱ ላይ ተብራርቷል።

ይህ የባንኩ አዲስ ንቅናቄ ዳያስፖራው በሀገሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የባንኩ መረጃ ያመላክታል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: