በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ ከተማ የተገነባው የመሶብ የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋም በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደተናገሩት፣ በተለያዩ ሴክተሮች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው የነበሩ ችግሮች ሕዝብን እና መንግሥትን አራርቀው የቆዩ ነበሩ።
ይሁን እንጂ በዚሁ የመሶብ አንድ ማዕከል አማካኝነት በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ የነበረውን መስተጓጎል በማስቀረት ለሕዝቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱንና ችግሮቹ መቃለላቸውን ገልጸዋል።
የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፋት እንዲሁም ምቹ የአገልግሎት ማዕከላትን ለመፍጠር ያለመው ይህ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ በሀገራችን በየአካባቢው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ሥራውን በይፋ የጀመረው የዲላ መሶብ ማዕከል 12 ተቋማትን እና 41 የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ጥላ ሥር አስተባብሮ የያዘ ነው።
በክልሉ የመሶብ አንድ ማዕከል የማዳረስ ሥራ በትኩረት እንደሚቀጥል የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ኅብረተሰቡ በሁሉም ዘርፍ የመንግሥት ሥራዎች ተቀናጅተው እንዲሠሩ ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሕዝባችን የከበረ አገልግሎት ያስፈልገዋል በሚል እምነት መንግሥት የጀመረው በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል የመስጠት አሠራር በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ መሠረታዊ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማ መዋቅር የመጀመሪያው የሆነው ይህ የዲላ ማዕከል ከመመረቁ በፊት፣ በክልሉ በወላይታና በአርባምንጭ ከተሞች አገልግሎቱ ተጀምሮ ለኅብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የዲላ ከተማ ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር)፤ በከተማዋ ባለፈው በጀት ዓመት የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ማስቀረት የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ ለዚህ ውጤት የከተማው ሕዝብ ያደረገው ትብብር የሚደነቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን አብራርተዋል።
ከዚሁ የመሶብ አንድ ማዕከል ምረቃ ጎን ለጎን ዘመናዊ የመንገድና የጎዳና መብራት ዝርጋታዎች፣ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የአንድ መንደር ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የተዘጋጁ የማምረቻና መሸጫ ሼዶችን ጨምሮ ሌሎች የተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: