Search

በመደመር ዕሳቤ ከፍታዋን እያረጋገጠች ያለችው ኢትዮጵያ

እሑድ ነሐሴ 10, 2018 138

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም በከፍተኛ የዕድገት እና ፈጣን የልማት ማዕበል ውስጥ ትገኛለች።

በተለይም ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የኢንዱስትሪ እና የግብርና ልማት ምርታማነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው።

በምግብ ራስን ከመቻል አኳያ በተያዘው ሀገራዊ መርሐ ግብር በስንዴ ልማት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በሌማት ትሩፋት እየተመዘገቡ ያሉ ተጨባጭ ስኬቶች የኢኮኖሚያዊ እና የማኅበራዊ ሕይወት ገጽታችንን እጅጉን እያሻሻሉት ይገኛል።

ከውጭ የሚገባን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራችንም የዚሁ ስኬት ማሳያ ነው።

ከመዲናችን አንሥቶ በተለያዩ ክልል ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተሞችን ውበት ከመቀየር እና የሌሊት ኢኮኖሚን ከማነቃቃት ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ ዘመናዊ አካባቢን እየፈጠሩ ይገኛሉ።

ከዚህ የከተሞች መሻሻል ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም በሚገባ እያወጡት ያሉት 'ገበታ ለሀገር' ፕሮጀክቶች ተዘንግቶ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርገውታል።

በሌላ በኩል 'አረንጓዴ ዐሻራ' መርሐ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የተመዘገበው ስኬት ከደን ልማትነቱ አልፎ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ፣ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ እና የዲፕሎማሲ አቅም ማሳያ እየሆነ ነው።

የማዕድኑ ዘርፍ ከብክነት እና ሕገ ወጥነት ተላቅቆ የኢኮኖሚው ምሰሶ እየሆነው መምጣቱን በወርቅ ብቻ የተገኘው ገቢ ትልቅ ማሳያ ነው።

በቴክኖሎጂው ዘርፍም የነገዋን ኢትዮጵያ በትውልዱ አዕምሮ ውስጥ ለመገንባት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው።

በተለይም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭን በመሳሰሉ ፕሮግራሞች ከዓለም ቀዳሚዎች ጋር ለመፎካከር በተያዘው ራዕይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ፋና ወጊነቷን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለች።

እነዚህን ሁሉ አዎንታዊ ለውጦች በማምጣት መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ማድረግ የተቻለው 'መደመር' በሚለው ሀገራዊ የመሪ ሐሳብ ነው።

መደመር ያለፉ መልካም ዕሴቶችን በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እና የነገን ብሩህ ተስፋ በመሰነቅ የተቃኘ የትውልድ ድልድይ ነው።

ይህ ዕሳቤ እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ ሀገራዊ አቅሞችን እና ዕውቀቶችን በማስተባበር እንዲሁም ልዩነቶችን ወደ ውበት በመቀየር ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የዕድገት እና የሥልጣኔ ምዕራፍ አሸጋግሯታል።

የመንግሥት የላቀ ቁርጠኝነት እና የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ተቀናጅተው መሥራታቸው ለዚህ ዘርፈ ብዙ ውጤት ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል።

ይህ ታላቅ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የዕድገት ተምሳሌት፣ የጽናት ማሳያ እና የብልጽግና ተስፋ አድርጎ አጉልቶ አውጥቷታል።

ዛሬ እየተጣሉ ያሉ ዘላቂ መሠረቶች እና በየዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ አበረታች ስኬቶች የነገዋን ጠንካራ፣ ነጻ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርጉ ናቸው።

በመሆኑም ሁላችንም በኅብረት፣ በአንድነት እና በወንድማማችነት በመቆም እንዲሁም የመደመርን ሐሳብ በተግባር በማዋል የጀመርነውን የታላቅነት እና የብልጽግና ጉዞ አጠናክረን በመቀጠል ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ እናሸጋግራለን።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: