በአውሮፓውያኑ 2007 በአፍሪካ ኅብረት የተበሰረው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ የአህጉሪቱን የተራቆተ መልክዓ ምድር አረንጓዴ በማልበስ በሳህል ቀጣና የሚኖሩ ሚሊዮኖችን ሕይወት የመለወጥ ታላቅ ራዕይ ሰንቆ የተነሳ ፕሮጀክት ነው።
በፕላኔታችን ላይ ካሉት የሥነ-ሕይወት ፕሮጀክቶች ሁሉ ትልቁ እንደሆነ የተነገረለት እና በአፍሪካ ውስጥ 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ ግድግዳ በአሁኑ ወቅት የዛፍ ተከላ ፕሮጀክት ከመሆን አልፎ የማኅበረሰብን ኢኮኖሚያዊ አቅም ወደ መገንባት ተሸጋግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በረሃማነትን የመዋጋት ኮንቬንሽን (UNCCD) የዘንድሮ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፕሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አረንጓዴ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
ከምንም በላይ ደግሞ ማኅበረሰቡ ተፈጥሮን በመንከባከብ የገቢ ምንጭ ማግኘት እንደሚችል ግንዛቤ በመፈጠሩ ሁለንተናዊ ተሳትፎው እያደገ መጥቷል።
የፕሮጀክቱ ዋና ግብም በአውሮፓውያኑ 2030 ወደ በረሃማነት የተለወጠውን 100 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ወደ አረንጓዴነት በመመለስ 250 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ማመንጨት ነው።
ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ አደገኛነት ቀድማ የተረዳችው ኢትዮጵያ ይህንን የአህጉር ራዕይ ከግብ ለማድረስ እጅግ ፈጣን እና ፈር ቀዳጅ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በመጠበቅ ምርት እና ምርታማነትን የሚያጎለብት፣ እንዲሁም ብልፅግናን ለመጪዎቹ ትውልድ የሚያስቀጥል ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው አዲስ መረጃ መሠረት መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዘንድሮውን ተከላ ጨምሮ 56 ቢሊዮን ገደማ ችግኞች ተተክለዋል። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ይህን ቁጥር 65 ቢሊዮን ለማድረስ ገብ ተይዟል።
ይህ ቁጥር ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ትግል ውስጥ ያላትን ቁርጠኝነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
የተተከሉ ችግኞችን ማሳደግ ትልቁ የሥራው አካል በመሆኑ የችግኝ ተከላ ክትትል በዘመናዊ እና ሳይንሳዊ መንገድ መከታተል ተጀምሯል። በዚህም የችግኞቹ የጽድቀት መጠን ከ82 በመቶ በላይ መድረሱን ለማረጋገጥ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ለተፈጥሮ ጥበቃ እና ለግብርና ልማት ላበረከተችው የላቀ አስተዋጽዖም ከዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ተሸላሚ በመሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝታለች። በተጓዳኝም የለም አፈር መከላትን በእጅጉ ከመቀነሱም በላይ የደን ምንጣሮን በከፍተኛ ሁኔታ መግታት ተችሏል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት ከኢትዮጵያ አልፎ አህጉራዊ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሯል። የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ልምድ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች እየወሰዱት ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የራሷን መልክዓ ምድር አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በስጦታ በመስጠት የአፍሪካ ተምሳሌትነቷን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
በመርሐ ግብሩ ግብርናን ታሳቢ ያደረጉ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ እና ሌሎች የጥቅም ዛፎች ላይ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱ የውጭ ምንዛሬን ማምጣ እስከመቻል የደረሰ ውጤት አምጥቷል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2030 አሁን ያለውን የ23.6 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ጠንካራ ስትራቴጂ ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ይህንን ትልቅ ግብ የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ እ.አ.አ በ2030 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ካስቀመጠው ራዕይ ጋር ስናነጻጽረው የኢትዮጵያ እርምጃ እጅግ ፈጣን መሆኑን እንረዳለን።
የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ ዒላማውን እንዲመታ ኢትዮጵያ በምታደርገው የተግባር ልቀት ቀድማ እየተጓዘች እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊከተሉት የሚገባውን መንገድ እያሳየች ትገኛለች።
መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያውያን በየጓሮአቸው ችግኞችን ተክለው የሚንከባከቡበትን ባህል የፈጠረ ሲሆን፣ ለነገው ትውልድ የምትተላለፍ አረንጓዴ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: