Search

በአማራ ክልል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ወደ ዲጂታል ሥርዓት ገባ

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 150

የመደመር መንግሥት ትኩረት የሰጠው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አካል የሆነው የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ የማሰባሰብ፣ የማጥራት እና ወደ ዲጂታላይዝድ ቋት የማስገባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ይህ አሠራር የተደራጀ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃን በመያዝ ፈጣንና ግልጽነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፣ የመንግሥትን በጀት ከብክነት ለመታደግ ከፍተኛ ሚና አለው።

በዚህም መሰረት በአማራ ክልል ከሚገኙ 500 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ እስካሁን በነበረው ሂደት 80 በመቶ ሠራተኞችን መረጃ ማሰባሰብ መቻሉን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ / ካሳ አበባው ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት 432 ሺህ በላይ ሰራተኞች መረጃ ተሰብስቦ ወደ ሥርዓቱ ገብቷል።

የመንግሥት ሠራተኛን ትክክለኛ መረጃ በማደራጀት በአንድ ቋት ማስገባት እንደ ሀገር፣ ተቋም እና ግለሰብ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት / ካሳ፤ አሰራሩ በተለይም በሠራተኞች መረጃ ላይ የተመሰረተ ጥቅማጥቅም እና ደሞዝ በትክክል ለመወሰን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በክልሉ የተጀመረውን የመረጃ ማሰባሰብ እና የማጥራት ሥራ በወቅቱ ለማጠናቀቅ በየደረጃው በቅንጅት እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኞችም አስፈላጊ መረጃዎቻቸውን በማስመዝገብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

ይህ ሀገራዊ የመረጃ ማሰባሰብ እና የማጥራት ሥራ ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመተባበር እየተከናወነ የሚገኝ ነው።

በሳሙኤል ወርቃየሁ



 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: