የክረምቱ ጭጋግ እና ደመና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት፣ ሰማይ ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ ትውልድን ከትውልድ ያለፈውን ከዛሬው የሚያገናኝ ታላቅ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓል ነው - «ቡሄ»።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ የቡሄ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ በመውጣት መለኮታዊ ክብሩን እና ብርሃኑን የገለጠበትን ጥልቅ መንፈሳዊ ምስጢር ይዟል።
ሊቃውንት እና አባቶችም «ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት» በማለት የክረምቱ መገባደድ፣ የብርሃኑ እና የወገግታው መቅረብ የምስራች መሆኑን በምሳሌያዊ አነጋገር ይገልጹታል።
የጅራፍ ጩኸት፣ የ«ሆያ ሆዬ» ጭፈራ እና ሙልሙል ዳቦ የበዓሉ ማድመቂያዎች ናቸው።
የበዓሉ ሰሞን አዳጊዎች እና ወጣቶች ጅራፍ ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ። ይህም በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱ በተገለጠበት ወቅት የተሰማውን ታላቅ የመለኮት ድምፅ (ነጎድጓድ) እና የመብረቁን ብርሃን ለማስታወስ የሚደረግ የደስታ መግለጫ ነው።
የ«ሆያ ሆዬ» ጭፈራ ደግሞ የበዓሉ ሌላኛው ውበት ነው፤ አዳጊዎች በየደጁ «ሆያ ሆዬ» እያሉ በመጨፈር የምስራች ያበስራሉ። እናቶችም ለበዓሉ የተጋገረውን ሙልሙል ዳቦ ለሕፃናቱ በማደል የቆየውን የማጋራት፣ የፍቅር እና የበረከት ባህል ያጸናሉ።
ታዲያ በተለምዶ በቡሄ ሰሞን የልጆች የጅራፍ ጩኸት ከየአቅጣጫው እንደሚሰማው ሁሉ፤ ዛሬም ሀገራችን ኢትዮጵያ በተግባር የምታስተላልፈው የልማት እና የዕድገት ጥሪ ከከፍታ ላይ ይሰማል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና የኃይል ማመንጨት ስኬት፣ የባሕር በር መልሶ የማግኘት ጥረት፣ የሌማት ትሩፋት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ አዲስ የተስፋ ብርሃን መገለጫዎች ናቸው።
በበዓሉ ዋዜማ የሚበራው ችቦም የክረምቱ ጨለማ አልፎ የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ የሚያበስር የወደፊት የብርሃን አሻራችን ነው።
የዘመናችን ወጣቶችም ቡሄን በባህላዊ ጨዋታ እና በደስታ ብቻ ሳይሆን፤ በቴክኖሎጂ፣ በምርታማነት፣ በምግብ ዋስትና እና በ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያውያን የ«ኮዲንግ» ሥልጠና የወደፊት እጣ ፈንታውን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚደረግ ጉዞ ታግዘው ያከብሩታል።
ልጆቻችን ዛሬ በጋራ በመቆም “ከዚህ ቤት ይግባ በረከት” በማለት የሀገርን ዕድገት፣ ብልጽግና እና ኅብረተሰባዊ አንድነት ይመኛሉ።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: